ግልጸኝነትን በማስፈን የተቋሙን ገጽታ ለመገንባት አመራሩ ሚናውን መወጣት አለበት

ግልጸኝነትን በማስፈን የተቋሙን ገጽታ ለመገንባት አመራሩ ሚናውን መወጣት አለበት

ግልጸኝነትን በማስፈን የተቋሙን ገጽታ ለመገንባት በየደረጃው ያለው አመራር የድርሻውን መወጣት እንዳለበት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮምፕሊያንስና ገቨርናንስ ዘርፍ ገለጸ፡፡

የዘርፉ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አቶ ዱጉማ ነዳ እንደገለጹት የሥራ ባህሪያቸው በገቨርናንስ ዙሪያ ላይ ትኩረት ያደረጉ የሥራ ክፍሎችን በማስተባበር በተቋሙ ውስጥ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ለማስፈንና የተቋሙን ገጽታ ለመገንባት ዘርፉ በ2017 ዓ.ም እንደ አዲስ ተቋቁሟል፡፡

በተቋሙ መልካም የኮርፖሬት አስተዳደር በማስፈን የለውጥ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከግልጽነትና ከተጠያቂነት አንጻር መለወጥ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በክርክር ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን በመፈተሽና በክርክር የመርታት አቅምን በማሳደግ የክስ መዝገቦችን ለመቀነስ እንዲሁም የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን በመስጠትና የውይይት መድረኮችን በመፍጠር የሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተቋሙ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሚያደርጉ አሰራሮችን፣ መመሪያዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን በመፈተሸ የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በተለያዩ ጉዳዮች የሚፈረሙ ውሎች ሕግን የተከተሉ እንዲሆኑና ተቋሙን ለተለያዩ ጉዳቶች እንዳያጋልጡ የማረጋገጥ ሥራ በማከናወን የተቋሙን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲዘጋጁና እንዲፈረሙ እየተደረገ ነው፡፡

ውሎችን በአግባቡ አለማስተዳደር ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ በማድረግ ተቋሙን ለከፍተኛ ወጭ የሚዳርግ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው ያለው አመራር የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሚናን ተረድቶ ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን፣ ያስመዘገበውን ስኬትና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመግለጽ የተቋሙን ገጽታ በመገንባት በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡

የገጽታ ግንባታ ሥራውን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ የኮሙዩኒኬሽን ፖሊሲና ሌሎች ረቂቅ መመሪያዎች ተዘጋጅተው ለተቋሙ ሥራ አመራር መቅረባቸውን ያስታወሱት አቶ ደጉማ በቅርቡ ጸድቀው ወደ ሥራ ይገባሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን የተቋሙን ገጽታ መገንባት በየደረጃው ያለውን አመራሩ ቁርጠኝነትና ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም አመራር ሚናውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅበት አቶ ዱጉማ አሳስበዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top