በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአዋሽ ሁለትና ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ72 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ማምረታቸውን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ጌታቸው አበበ እንደተናገሩት በሩብ ዓመቱ በአዋሽ ሁለት 24 ነጥብ 6 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማምረት ታቅዶ 17 ነጥብ 65 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማምረት የዕቅዱን 71 ነጥብ 73 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡
በአዋሽ ሦስት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደግሞ 56 ነጥብ 32 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማምረት ታቅዶ 55 ነጥብ 25 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማምረት የ98 ነጥብ 11 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡
የአዋሽ ሁለት አፈጻጸሙ ዝቅ ሊል የቻለው ዓመታዊ ጥገና በሚከናወንበት ጊዜ በተርባይን ቤሪንግ ቫይብሬሽን ላይ የተከናወነው ጥገና ከታቀደው በላይ ጊዜ በመውሰዱ እና የክረምቱ የውሃ መጠን በማነሱ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ከዕቅዱ ዝቅ ያለ ቢሆንም በአዋሽ ሦስት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የተመረተው ኃይል ግን ካለፈው ሁለት በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የኃይል ምርት የ 6 በመቶ ብልጫ ያለው ነው ብለዋል።
ጣቢያዎቹ ከዕድሚያቸው አኳያ የመልሶ ግንባታ ሥራ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ ጌታቸው የታቀደውን ኃይል ለማማረት የሚያስችሉ የጥገና ሥራዎችን በማከናወን ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
የአዋሽ ሁለት እና ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እያንዳንዳቸው 32 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላቸው፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


