ችግሮችን በምክክር በመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል

ችግሮችን በምክክር በመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሥራ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ።

ከተቋሙ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ለተውጣጡ የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች የተሰጠውን ሥልጠና በንግግር የከፈቱት በተቋሙ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ ጌታቸው እንደገለፁት ለሚፈጠሩ ችግሮች ወቅታዊ መፍትሔ ለመስጠት ምክክር የማይተካ ሚና ይኖረዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ጤናማ የሆነ ምክክር በማድረግ ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

“የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ምክክር ለምርታማነት” በሚል ርዕስ ሥልጠናውን የሠጡት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የማህበራዊ ምክክር ባለሙያ አቶ ጌታቸው ታምሩ እንደተናገሩት  ሥልጠናው በቀጣይ በተቋሙ የሚካሄዱ ምክክሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በግብዓትነት ያግዛል።

ምክክሩ አሰሪውና ሠራተኛው በተቋሙ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ምርታማነትን ማዕከል ያደረገ የኢንዱስትሪ ግንኙነት እንዲፈጠር ያስችላል ብለዋል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ በምክክር ሂደቱ ላይ አሰሪ፣ ሠራተኛ እና መንግስት የሁለትዮሽና የሦሰትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።

የምክክር ሂደቱ “ከክርክር ወደ ምክክር፣ ከምክክር ደግሞ ወደ ምርታማነት” ለመሸጋገር ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ምክክሩ የተቋም ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን  ለማሳደግ፣ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ፣ የሥራ ባህል ለውጥ ለማምጣት፣ የአሰሪና ሠራተኛን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመለየትና መፍትሔዎቻቸውን ለማመላከት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመረጃና ዕውቀት አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ከበደ እና የተቋሙ መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር ፀሐፊ አቶ ኃይሉ ወልዴ በበኩላቸው ምክክሩ ሠራተኛው ለተቋሙ ምርታማነት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በውይይት በመለየት ለችግሮቹ የመፍትሔ አማራጮቹን ለማስቀመጥ ይረዳል ብለዋል።

በሥልጠናው ላይ የተሳተፉ ሠራተኞቸ እና የሥራ መሪዎች በየሥራ ክፍላቸው የሚካሄዱ ምክክሮችን በበላይነት እንደሚመሩ አስታውቀው ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆንም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ በምክክር ሂደቱና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የተቋማትን ምርታማነት ለማሳደግ “የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ምክክር ለምርታማነት” የሚል ስትራቴጅ ተቀርጾ እየተሰራ ሲሆን ምክክሩም ህዳር 16 ቀን 2017 ዓ. ም እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
ህዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Scroll to Top