የማመንጫ ጣቢያውን ደህንነት ለመጠበቅ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

የማመንጫ ጣቢያውን ደህንነት ለመጠበቅ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ደህንነት ለመጠበቅ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ጥሪ አቀረቡ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ እንደገለጹት ከወሰን አለመከበር እና ከስርቆት ጋር ተያይዞ የማመንጫ ጣቢያው ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል።

የጣቢያው ውሃው የሚተኛበት ቦታ ወይም ከሰዎች እና እንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆን የተከለለውን አካባቢ በማለፍ የግድቡ ውሃ በሚቀንስበት በበጋ ወራት የእርሻ ሥራ መበራከቱ የግድቡን ደህንነት አደጋ ላይ እየጣለ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህም ጣቢያው በደለል እንዲሞላ ከማድረጉም በላይ የግብርና ተረፈ ምረቱ ወደ ጣቢያው እየገባ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቴዎድሮስ እንቅስቃሴው ውሃ ወደ ጣቢያው እንዳያልፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ የግብርና ተረፈ ምርቱና ገለባው ወደ ጣቢያው የማቀዝቀዣ ማሽኖች በመግባት እንዳይሰሩ ከማድረግ ባለፈ የሚፈጠረው ሙቀት ዕቃዎቹን እስከ ማቅለጥ መድረሱን ተናግረዋል።

በዚህ የተነሳ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ ከሦስት ቀን በላይ እንዲቆም ማድረጉን እና የኦፕሬሽን ሥራ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ ከኃይል ማመንጫ ቤቱ እስከ ውሃ መቀበያው ወይም ኢንቴክ ያለው የመሬት ውስጥ መስመር እና ስዊች ያርዱንና ማመንጫ ቤቱን የሚያገናኙ መስመሮች ላይ የሚፈጸመው ስርቆትም ለጣቢያው ፈተና መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢው አባገዳ የሆኑት ሐጂ እንድሪስ ሐጂ ጉራሪ በበኩላቸው ማመንጫ ጣቢያው ለአካባቢው ማህበረሰብ የልማት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

የማመንጫ ጣቢያው መኖር ከተሞች እንዲስፋፉ፣ የመብራትና ውሃ አቅርቦት እንዲኖር፣ በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት እንዲከፈት በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

በመሆኑም የማመንጫ ጣቢያውን ወሰን አልፎ ከማረስ እና ከስርቆት ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አባ ገዳ ሐጂ እንድሪስ ገልጸዋል።

ከሚመለከታቸው የመስተዳድር አካላት እና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን የማመንጫ ጣቢያው ደህንነት ላይ ስጋት የደቀኑ ችግሮችን ለመፍታት መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top