የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት የሚከናወኑ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶች በፕሮጀክቶች ትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ እያገዘ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ገለፀ፡፡
የቢሮው ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋቀሳ ተሰማ እንደገለጹት ፕሮጀክቶች የሚገኙበትን አካባቢና የአካባቢውን የማህበረሰብ ደህንነት ለመጠበቅና ከለላ ለመስጠት ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት የአካባቢና ማህበረሰባዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶች ይከናወናሉ፡፡
ጥናቶቹ በሀገሪቱ ያሉ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎችን እንዲሁም የአበዳሪ ተቋማትን ፖሊሲና አሰራር መሰረት በማድረግ እንደሚከናወኑም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ዋቀሳ ገለፃ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶች ከፕሮጀክት ትግበራ ጋር ተያይዞ በአካባቢውና በማህብረሰቡ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለማስወገድ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
ጥናቶቹ በፕሮጀክት ትግበራ ጊዜ ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮቹ እንደ ጉዳት ዓይነት እና መጠን በዕቅድ ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያግዛል ብለዋል።
እየተከናወኑ ያሉ ጥናቶች ማህበረሰቡ በፕሮጀክቶች ዕቅድና አተገባበር ላይ እምነት እንዲኖረው በማድረግ የፕሮጀክቶችን ተቀባይነት እና አፈፃፀምን ከማሳደጉም ባለፈ በቀጣይ ለሚታቀዱ ሥራዎች በግብዓትነት እያገዘ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የጥናት ሥራው ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላትን እና ፕሮጀክቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በቅንጅት እንደሚከናወን ተወካዩ አመልክተዋል፡፡
በጥናቱ የተገኙ ውጤቶች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲደረጉ ፕሮጀክቱን ለሚተገብረው ቢሮ ሰነዱ እንደሚሰጥና ቢሯቸውም በአፈጻጸሙ ላይ ክትትል እንደሚያደረግ አስታውቀዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የ19 የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና 11 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ጥናት ለማከናወን መታቀዱን አቶ ዋቀሳ ጠቁመዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”