በገንዘብ ሚኒስቴር እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ስር የሚገኙ ከሰባት ተቋማት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና መስሪያ ቤትን ጎበኙ።
በጉብኝቱ ወቅት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉትን ሀብቶች ወደ ልማት በመቀየር ለሠራተኞቹ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ችሏል።
ተቋሙ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የኃይል አስተላላፊ ለመባል በቅቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በቀጣይም ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ ተቋሙ በራሱ አቅም በጎረቤት ሀገራት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዙሪያ የማማከር እና የመገንባት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኃይል ማመንጨት አቅም ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ የብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ እየተከናወነ እንደሆነም ነው የገለፁት።
ተቋሙ ከስያሜ ጀምሮ በርካታ ተግዳሮቶች እየገጠሙት እንደሚገኙ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከካሳ ክፍያ እና ከኃይል መሰረተ ልማት ስርቆት ጋር ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚመለከታቸው ሁሉ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ ለጎብኚዎች ስለ ተቋሙ ወቅታዊ አቋም ገለፃ አድርገዋል።
አቶ አንዱዓለም በገለፃው ላይ እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ዓመታት የሀገሪቱ የኢነርጂ ምርት በአማካይ የ8 በመቶ እንዲሁም የተቋሙ ዓመታዊ ገቢ በ34 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
በቀጣይ ዓመታት 825 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ስድስት የንፋስ እንዲሁም 775 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አምስት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አቶ አንዱዓለም ገልፀዋል።
እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በቀጣይ ሦስት ዓመታት 1 ሺህ 038 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና 27 አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመገንባት በ60 ኪሎሜትር ርቀት የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ወደ 91 በመቶ ለማሳደግ ይሰራል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቀጣዮቹ ዓመታት የአፍሪካ የኃይል የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ማቀዱንም ነው የጠቀሱት።
የገንዘብ ሚኒስትር ልዩ አማካሪና የጉብኝቱ አስተባባሪ አቶ ሐጂ ኢብሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሠራተኛው ምቹ የሥራ ቦታ ለመፍጠር ያከናወናቸው ሥራዎች የሚደነቁ በመሆናቸው ሌሎች ተቋማት ከዚህ ልምድ መውሰድ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ተቋሙ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ሥራዎችና በስትራቴጂክ ዕቅዶቹ ዙሪያ ስለተደረገላቸው ገለፃም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በጉብኝቱ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር፣ ከኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕና ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የተውጣጡ ከ400 በላይ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





