የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ወጪን ተቋሙ በራሱ ገቢ እየሸፈነ ነው

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ወጪን ተቋሙ በራሱ ገቢ እየሸፈነ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ከፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር ተያይዞ የሚታዩበትን ውሱንነቶች ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር አስታወቀ፡፡

አስተዳደሩ የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ከኃይል ሽያጭ፣ ከተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች፣ ከታሪፍ ማሻሻያ፣ ከፕሮጀክቶች አፈፃፀምና ከፋይናንስ እንዲሁም ከሥርዓተ ፆታ ስብጥር አንፃር ገምግሟል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት የተቋሙን ስምና አርማ ለመቀየር እና የካፒታል መጠኑን ለማሳደግ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ደንቦች ተዘጋጅተው ወደሚመለከታቸው አካላት ተልኳል።

መንግሥት የተቋሙን የሀገር ውስጥ ዕዳ በከፊል መሰረዙን እና ቀሪ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ብድር ዕዳን ለመክፈል የሚያስችል ታሪፍ እንዲኖር እየተሰራ በመሆኑ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታን ባለበት ፍጥነት ለማስቀጠል ከኃይል ሽያጭ ገቢ ላይ በየወሩ 5 ሚሊየን ዮሮ እየተከፈለ ይገኛል።

በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ ለታንዛኒያ ሊቀርብ የታሰበው የኃይል ሽያጭ በታቀደው ጊዜ ባለመጀመሩ የውጭ የኃይል ሽያጭ አፈፃፀም ቀንሷል።

በኬንያ እና ታንዛኒያ መካከል ያለው ሥምምነት በቅርቡ እልባት ስለሚያገኝ የኃይል ማስተላለፊያ ኮሪደሩ እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ኤሌክትሪክ ለማስተላለፍ አመቺ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በተቋሙ የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ውድነህ የማነ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የፕሮጀክቶችን የግንባታ አፈፃፀም ለማሻሻል ታቅዶ እየተሰራ ቢሆንም ከፀጥታና መሰል ችግሮች ጋር በተያያዘ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ከመሰረተ ልማት ስርቆትና ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እገዛ ማድረግ አለባቸው።

በተቋሙ የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንዳሉት ደግሞ ተቋሙ ከኃይል ሽያጭ ገቢ በርካታ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን እየገነባ ይገኛል።

ተቋሙ አጠቃላይ ሀብቱ 719 ቢሊየን ብር እንዲደርስ መንግሥት፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የሥራ አመራር ቦርዱ እና አስተዳደሩ ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ለተደረገው እገዛም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተቋሙ የንብረት አስተዳደር ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ስመኝ አያሌው በበኩላቸው በ2016 በጀት ዓመት የሸገር ከተማ አስተዳደር በውስጡ ለሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዓመታዊ የይዞታ ግብር የጠየቀው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን እልባት እንዲያገኝ ጉዳዩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መድረሱን ተናግረዋል።

በተቋሙ የሰው ኃይል አስተዳደር ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ በበኩላቸው በተቋሙ ከሥርዓተ ፆታ ስብጥር እና የማሰልጠኛ ማዕከላትን ከማስፋፋት ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

በግምገማው ላይ የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ተወካይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ይርጋ እንደገለፁት በየሩብ ዓመቱ የሚደረገው ግምገማ የተቋሙን ውጤታማነት ለማሻሻል ያግዛል።

ተቋሙ በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከኃይል ሽያጭ ያልተሰበሰቡ ገቢዎችን በመሰብሰብና አማራጭ የገቢ ማግኛ አማራጮችን በማስፋት አቅሙን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

ከፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ማረጋገጫ የሰጡት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top