በጣቢያው ጥገናዎችን በራስ አቅም የማከናወን ልምምድ እያደገ መጥቷል

በጣቢያው ጥገናዎችን በራስ አቅም የማከናወን ልምምድ እያደገ መጥቷል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በግልገል ጊቤ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጥገናዎችን በራስ አቅም የማከናወን ልምምድ እያደገ መምጣቱን የጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ ገለጹ።

ኃላፊው አቶ አሸናፊ ተስፉ እንደተናገሩት ከአሁን ቀደም በጣቢያው ከፍተኛ ውጪ ወጥቶባቸው በውጭ ሀገር ባለሙያዎች ብቻ ይከናወኑ የነበሩ የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም እየተከናወኑ ነው።

ጣቢያው በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዲያመነጭ የሚያስችሉ ከቅድመ መከላከል ጀምሮ የትንበያ እና የሁኔታ አመላካች የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም የጣቢያው አራቱም ተርባይኖች ውሃን ለመቆጣጠር የሚያገለግለው ሹል ጫፍ ያለው የብረት አካል ወይም ኖዝሎች በመበላታቸው ምክንያት የአንድ ተርባይን የማመንጨት አቅም ከ105 ሜጋ ዋት ወደ 25 ሜጋ ዋት ቀንሶ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

በኃይል ማመንጫ ጣቢያው ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ላይ የዋሉ የተርባይን ፓዎር ኖዝሎች በራስ አቅም የጥገና ሰራዎችን በማከናወን ተርባይኖቹ በሙሉ አቅማቸው 105 ሜጋ ዋት እንዲያመነጩ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የተበሉ ካርበን ብረሾችን በአዲስ የመተካት፤ የስዊችያርድ፣ የመቆጣጠሪያ ክፍል እና የመሳሰሉት የሙቀት መጠን የመቆጣጠር እና የማቀዝቀዣ መሳሪያዎች እንዲሁም ሌሎች የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

ይህም ጣቢያው በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዲያመርት ከማስቻሉም በላይ ጊዜንና ወጭን በመቀነስ በኩል ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የጥገና ሥራው በራስ አቅም መከናወኑ ተቆሙ ያሉትን ባለሙያዎች አቅም ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀም እድል የፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አሸናፊ ሠራተኞች ሙያዊ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ትልልቅ የጥገና ሥራዎችን መስራት እንችላለን የሚል የራስ መተማመን እንዲኖራቸው አስችሏል ብለዋል።

የጣቢያው የጥገና ባለሙያ መልካም ባወቀ በበኩሏ በጣቢያው ከተቀጠረች ሁለት ዓመት ቢሆናትም በራስ አቅም በተከናወኑ የሁለት ተርባይኖች ኖዝል ሥራ ላይ መሳተፏን ገልጻለች።

ይህም እሷ እና ሌሎች አዳዲስ የጥገና ባለሙያዎቹ ተግባር ተኮር ዕውቀት ያገኙበትና ትልልቅ የጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል ትምህርት የወሰዱበት መሆኑን ተናግራለች።

በጣቢያው የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ሽመልስ አዱኛ እንደገለጸው በጣቢያው በራስ አቅም የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የኦፕሬሽን ሥራውን በማሳለጥ በኩል ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

ቀደም ሲል በተርባይኖቹ ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የኦፕሬሽን ሥራዎችን ከአንድ ማዕከል ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎት መቆየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የኦፕሬሽን ባለሙያዎች በማንዋል ቁጥጥር ለማድረግ አስገድዷቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በተርባይኖቹና በጣቢያው ማሽኖች ላይ በራስ አቅም የተከናወነው የጥገና ሥራ ጣቢያው በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዲያመነጭ ከማድረጉም ባሻገር የኦፕሬሽን ሥራውን ከአንድ ማዕከል መቆጣጠር አስችሏል ብለዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top