ከቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ ባለ 132/33/15 ኪሎ ቮልት ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ ሲያገኙ ለነበሩ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ሁለት ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ ገለፀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ዘበርጋ እንደገለፁት በጊዜያዊነት ታስቦ የተቀመጠው የተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ9 ዓመት በላይ አስቆጥሯል።
50 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው ትራንፎርመር የተገጠመለት የተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን መገንባቱን ተከትሎ ኃይል መስጠት መጀመሩን አስታውሰዋል።
ጣቢያው በአሁኑ ወቅት ለቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን፣ አራብሳ፣ ሰሚት፣ ክሬሸር፣ ጎሮ እና አካባቢው ከ34 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝም ነው ዳይሬክተሩ የጠቀሱት።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ በቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት ባለ 230/33/15 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የተከናወነው የማስፋፊያ ሥራ ለኢንዱስትሪ ዞኑና ለአካባቢዎቹ በቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያስችላል።
ቀደም ሲል የቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን ይጠቀሙ የነበሩ አካባቢዎችን መስመር በመቀየር ከቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት የማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነውም ብለዋል።
የቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ማህሌት ታዬ እንደተናገሩት ጣቢያው አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ገቢ እንዲሁም በ33 ኪሎ ቮልት ሁለት እና በ15 ኪሎ ቮልት አራት ወጪ መስመሮች አሉት።
እንደ ወ/ሮ ማህሌት ገለፃ በአሁኑ ወቅት ከተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ኃይል ሲያገኙ የቆዩ አካባቢዎች በቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት የኃይል ማከፋፈያ ስር እንዲጠቃለሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በማያመች ቦታ ላይ እንደተቀመጠ የገለፁት ሥራ አስኪያጇ የሠራተኞችን እና የጣቢያውን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ትኩረት እንዲሰጠውም አሳስበዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”