የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች የሰመራ ማከፋፈያ ጣቢያን ጎበኙ

የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች የሰመራ ማከፋፈያ ጣቢያን ጎበኙ

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ከአፋር ክልል የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች የሠመራ ባለ 230/33 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን ጎብኝተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ውቤ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአፋር ክልል የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አህመድ ሁሴን፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን እና ሌሎች የክልሉና የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች የጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራዎች እና በጣቢያው እየተከናወነ ያለውን ተጨማሪ የሸንት ሪአክተር ተከላ ሥራ ተመልክተዋል።

የሠመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ኢንድሪስ አህመድ ለሥራ ኃላፊዎቹ ገለፃ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ጣቢያው አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ፣ ስድስት ባለ 33 እና ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት።

ጣቢያው ከኮምቦልቻ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ ለሠመራ፣ ሎጊያ፣ ሚሌ፣ ዱብቲ ፣ አሳይታ ከተሞችና ለሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ33 ኪሎ ቮልት እንዲሁም ለዲቼቶ እና አፍዴራ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በባለ 230 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ኃይል እያቀረበ እንደሆነ አስረድተዋል።

በማከፋፈያ ጣቢያው የተተከለው 25 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር እስከ 20 ሜጋ ዋት ኃይል እየጫነ እንደሆነም ተናግረዋል።

በአፍዴራ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ያለውን የኃይል መዋዠቅ ለማመጣጠን በሠመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ተጨማሪ የሸንት ሪአክተር ተከላ ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአፋር ክልል የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አህመድ ሁሴን ተቋሙ በክልሉ ያለውን የኃይል ተደራሽነት ለማስፋፋት እያደረገ ያለውን ጥረት አመስግነዋል።

በቀጣይ የህብረተሰቡን የኃይል ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስና የክልሉን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ተቋሙ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሠሜን ምስራቅ 2 ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሀሰን መሀመድ በበኩላቸው በክልሉ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በአፍዴራ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ባለው የኃይል ተጠቃሚ ማነስ ምክነያት የኃይል መዋዠቅ እንደሚስተዋል ያነሱት ዳይሬክተሩ ይህም ከጣቢያው ኃይል የሚያገኙ አካባቢዎች አስተማማኝ ኃይል እንዳያገኙ እያደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ሀሰን ገለፃ በሠመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ እየተከናወነ ያለው ተጨማሪ የሸንት ሪያክተር ተከላ ሥራ ከአፍደራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል የሚያገኙት ኢሬፕቲ፣ አፍዴራ፣ ቢዱ እና ኩሪ የተሰኙ ወረዳዎች የ24 ሠዓት የኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባለፈ በሰመራ ማከፋፈያ ጣቢያ፣ በግሪዱና በብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከሉ ላይ የተረጋጋ ኃይል እንድኖር ለማድረግ ያግዛል።

በአሁኑ ወቅት 10 የክልሉ ተወላጆች በሪጅኑ በሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በማከፋፈያ ጣቢያ ኦፕሬተርነት በልዩ ሁኔታ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንና በቀጣይ ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ውቤ በበኩላቸው በክልሉ የሚነሱ የኃይል ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመመለስ ተቋሙ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሠመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ እየተከናወነ ያለው የሸንት ሪያክተር ተከላ ሥራ የክልሉን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወነ ላለው ሥራ አንዱ አካል እንደሆነም ጠቁመዋል።

በቀጣይ የሠመራ ማከፋፈያ ጣቢያን አቅም በማሳደግ እና የመቆጣጠሪያ ብሬከሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመቀየር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

በክልሉ የሰሜኑ ክፍል የሚነሱ የኃይል ጥያቄዎች በቀጣይ ሊከናወኑ ከታሰቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን የተቋሙን የፋይናንስ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እንደሚመለሱና ተቋሙም ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ ሀብታሙ አረጋግጠዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top