በአፋር ክልል እየተፈፀመ ያለውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ለማስቆም ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አሳሰቡ።
በክልሉ እየተፈፀመ ያለውን የኃይል መሰረተ ስርቆት ለመከላከል ከክልሉ፣ ከአውሲ ረሱ ዞን፣ ከዱብቲ፣ ሚሌና አዳአር ወረዳዎች፣ ከሰመራና ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ አመራሮችና የፀጥታ አካላት እንዲሁም ከጎሳ መሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አህመድ ሁሴን እንደተናገሩት የኤሌክትሪክ ኃይል ለክልሉ ማህበረሰብ ለልማት ብቻ ሳይሆን ለእስትንፋሱም ፋይዳው የጎላ ነው።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት በማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መጥቷል ብለዋል።
በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል በየደረጃው ያለው የክልሉ አመራር፣ የፀጥታ አካላት እና ማህበረሰቡ በቅንጅት በመስራት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።
የአፋር ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው ኤሌክትሪክ ለክልሉ ማህበረሰብ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ አመራሩ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ለመከላከል ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ማህበረሰብ እንደ መጤ ባህል የሚቆጠረው የስርቆት ድርጊት እንዳይስፋፋ ሁሉም ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ሊታገለው እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ እንደገለፁት የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል በአቀባይና ተቀባይ መካከል ያለውን ሰንሰለት መበጠስ ያስፈልጋል። ለዚሁ ደግሞ የሁሉምን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ነው ያስረዱት።
በስርቆት የተጠረጠሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል ከሚመለከተው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የአውሲ ረሱ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ሃመዱ መድረኩ ችግሩን በተናበበ መልኩ ለመከላከል ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው እየተፈፀመ ያለውን ስርቆት ለመከላከል በዞን ደረጃ አመራር ተሰጥቶበት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ውቤ እንደገለፁት ተቋሙ በክልሉ ያለውን የኃይል ተደራሽነት ለማስፋፋት ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ነው።
ይሁን እንጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመሠረተ ልማቶቹ ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ስርቆቶች ተቋሙ የኃይል መሠረተ ልማቱን ለማስፋፋት በሚያከናውነው ሥራ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የኃይል መሰረተ ልማት ስርቆትን ለማስቀረት የተለያዩ ሥራዎችን ቢያከናውንም መፍትሔ እንዳልመጣ ነው የተናገሩት።
በዚህም ተቋሙ በክልል በየደረጃው ከሚገኙ አመራርሮች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል በሁሉም አካባቢዎች ውይይቶችን እያካሄደ እንደሆነ እና መሠረተ ልማቱን የሚከታተልና ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ክፍል ማዋቀሩንም አስታውቀዋል።
በክልሉ የሚስተዋሉ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አመራሮች ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በተቋሙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆትን ለመከላከል በየደረጃው ያለው አመራር መሰረተ ልማቶችን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ተገንዝቦ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።
ከቅድመ መከላከል ሥራው ጎን ለጎን የፍትህና የፀጥታ አካላት በመሠረተ ልማት ስርቆት የተሳተፉ ወንጀለኞች ላይ አስተማሪ ቅጣት እንዲወስዱም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ ጌታቸው እንደተናገሩት የአፋር ክልል የኃይል መሠረተ ልማቱን ለመጠበቅ እየተከተለ ያለው አሰራርና እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚበረታታና ለሌሎችም ተሞክሮ የሚሆን ነው።
ሁሉም ለመሠረተ ልማቱ ደህንነት ዋስትና ሆኖ እንዲሰራ የእኔነት ስሜት ያለው ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚጠይቅ እና የዳጉ ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተቋሙ የሰሜን ምስራቅ 2 ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሀሰን መሀመድ ስለ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ገፅታና ባለፈው አንድ አመት በሪጅኑ ስለተፈፀሙ የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ሞሰሶዎች ስርቆት መጠንና ስርቆቱ በየትኞቹ አካባቢዎች እንደሚስተዋል በውይይቱ ወቅት ገለፃ አድርገዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”