ስርቆትን ለመከላከል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሊሰራ ይገባል

ስርቆትን ለመከላከል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሊሰራ ይገባል

በአፋር ክልል በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ስርቆት ለመከላከል ህብረተሰቡን ባሰተፈ መልኩ እንደሚሰሩ ከክልሉ፣ ከአውሲ ረሱ ዞንና ከተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት እና የጎሳ መሪዎች ጋር በተካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፉ የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቢልኤ አህመድ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው የስርቆት ወንጀል የብሄራዊ ደህንነት ስጋት እየሆነ መጥቷል።

ከዚህ በፊት በስርቆት የወደመውን ንብረት መመለስ ባይቻልም ውድመቱ እንዳይቀጥል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

“ስርቆትን መከላከልና የሀገርን ሀብት መጠበቅ ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ማህበረሰብ ኃላፊነት አለበት” ያሉት ኮሚሽነሩ ለዚህም ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን መሃመድ በበኩላቸው በመሰረተ ልማቶቹ ላይ እየተፈፀመ የሚገኘውን የስርቆት ወንጀል ለማስቆም በየደረጃው ከሚገኙ የተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለመሠረተ ልማት ስርቆት ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እንደ ክልል ቁርጥራጭ ብረቶቹን የሚገዙ ነጋዴዎች በክልሉ እንዳይሰማሩ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።

በክልሉ የሚፈጠሩ የስርቆት ችግሮችን ለመፍታት የፀጥታ አካላት ኃላፊነት ወስደው እንደሚሰሩ ገልፀው ይህ ውጤታማ እንዲሆን ማህበረሰቡና ተቋሙ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ እንደተናገሩት የክልሉ ማህበረሰብ አኗኗር የተበታተነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሠረተ ልማቱን በቅርበት ለመጠበቅ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል።

ይሁንና ማህበረሰቡ በኃላፊነት ጥበቃ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ ላይ አመራሩ የግንዛቤ ማስጨመጫዎችን በስፋት መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የአውሲ ረሱ ዞን ብልፅግና ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ሃመዱ በበኩላቸው ማህበረሰቡ መሠረተ ልማቱን በኃላፊነት እንዲጠብቅ፣ ስርቆቱ በሀገር ኢኮኖሚ እና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በሚከናወነው ሥራ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በማስገንዘብ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ለህብረተሰቡ አገልግሎት በሚሰጡ የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ለመከላከል ከአማራ ክልል የአጎራባች ወረዳዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የአጎራባች አካባቢዎችም ከዞኑ ማህበረሰብ ጋር ተቀናጅተው በመስራት የስርቆት ወንጀሎችን በትብብር እንዲከላከሉ አቶ ናስር ጥሪ አቅርበዋል።

የስርቆት ድርጊቱ የክልሉ መገለጫ እንዳይሆን የፀጥታ ኃይሉ ህብረተሰቡን በማንቃት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ እና ማህበረሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ኃላፊዎቹ አሳስበዋል።

እንደ ሥራ ኃላፊዎቹ ገለፃ ውይይቱ ለስርቆት ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ጥበቃ የሚደረግበትን አግባብ እና የመረጃ ልውውጡ የሚካሄድበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ዕድል ይፈጥራል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top