በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ በተቋሙ ባላቸው የአመራርነት ሚና እና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦ የኢነርጂ ዘርፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ በሚል ዕውቅናና ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ኢነርጂ ማህበር በኢነርጂ ዘርፍ ላይ በፈጠራና በአስተዳደር እንዲሁም በልዩ ልዩ ደረጃዎች ተፅዕኖ ለፈጠሩ ሴቶች ዕውቅና ለመስጠት እና በኢነርጂ ዘርፍ ላይ የተሳተፉ ተቋማትና ድርጅቶች ምርታቸውንና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት አውደ ርዕይ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል፡፡
በዕለቱም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤን ጨምሮ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለሆኑ ተጨማሪ ሁለት ሴቶች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ዕውቅናውን የሰጡት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት የኢነርጂ ዘርፍ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል፡፡
ዘርፉን ለማሳደግ ብቃት ያለው እና በሁሉም ጾታዎች የተመጣጠነ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ገልፀው ሚኒስቴሩም ሴቶችን ወደ ዘርፉ ለማምጣት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ያለውን የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ብቃት ያለው ባለሙያ ለመፍጠር እየሰራ ካለው ሥራ ጎን ለጎን በዘርፉ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሴቶችን ዕውቅና ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት አመስግነው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለማህበሩ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ኢነርጂ ማህበር ፕሬዚዳንት እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ ዘርፍ የሱፐርቪዥንና ኮንትራት አስተዳደር ቢሮ ሪዚደንት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት አደይ ጌታቸው በበኩላቸው ማህበሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢነርጂ ዘርፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለሆኑ ዘጠኝ ሴቶች ዕውቅና መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በተካሄደው መርሃ ግብር ከቀረቡ አስር ተወዳዳሪዎች መካከል ለሦስት የኢነርጂ ዘርፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዕውቅናና ሽልማት መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡
ዕውቅናዉ ሴት ባለሙያዎች በኢነርጂ ዘርፍ የሚያደርጉትን አስተዋጽዖ ለማስተዋወቅ፣ ለማበረታታት እና ለማክበር እንዲሁም ወጣት ሴቶች በዘርፉ እንዲሰማሩና ለሌሎች ዓርአያ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ ማህበሩ ላበረከተላቸው ዕውቅና አመስግነው ዕውቅናው በተቋሙ ባላቸው የአመራርነት ሚና፣ የተቋሙን ሴት ሠራተኞች ጫና ለማቃለል እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል::
ዓላማን ለማሳካት ዛሬ ከትላንት የተሻለ እንደሆነ በመገንዘብና ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በትጋት መስራት እንደሚጠበቅ የተናገሩት ወ/ሮ ሌንሴ የተሻለ ነገር ለማግኘት ሴቶች ያላቸውን አቅም አሟጠው መጠቀም እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ኢነርጂ ማህበር (EWiEN) በኢነርጂ ዘርፍ ያለውን የሥርዓተ-ፆታ ክፍተት ለማመጣጠን በማሰብ በአምስት ሴት ባለሙያዎች የተመሠረተ ለትርፍ ያልተቋቋመና መንግሥታዊ ያልሆነ ማህበር ነው፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
ህዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም