የሰመራ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ትራንስፎርመር በመሙላቱ የተነሳ ጣቢያው በአግባቡ አገልግሎት ለመስጠት መቸገሩን የሰሜን ምስራቅ 2 ሪጅን አስታወቀ።
የሪጅኑ ዳይሬክተር ሀሰን መሀመድ እንደገለፁት በጣቢያው የተተከለው ባለ 25 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመር መጫን ከሚችለው አቅም በላይ ኃይል እየጫነ ነው።


በዚህ የተነሳ ሰመራ፣ ዱብቲ፣ አሳአይታ፣ ሚሌ፣ ሎጊያና በአቅራቢያቸው የሚገኙ ከተሞች ጭነት በሚበዛባቸው ሰዓታት በጊዜያዊነት ኃይል በፈረቃ ለመስጠት እየተገደዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሀሰን ገለፃ በአካባቢው የኃይል ፍላጎት በፍጥነት እያደገ መምጣቱ፣ በአካባቢው ባለው ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ የአየር ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች አጠቃቀም መጨመሩና የኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ ኃይል መፈለጉን ለተፈጠረው ችግር እንደምክንያት ጠቅሰዋል።
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አራት እና አምስት ሜጋ ዋት ብቻ ይጭን የነበረው ጣቢያው በአሁኑ ሰዓት እስከ 23 ሜጋ ዋት ለመጫን በመገደዱ በጣቢያው ትራንስፎርመር ላይ ከፍተኛ ጫና መፈጠሩን አስታውቀዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ቴክኒካዊ መፍትሔዎች እየታዩ በመሆኑ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ አቶ ሀሰን ጠይቀዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
