በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ኢትዮጵያን ብርሃን የማልበስ ዓላማ ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዙሪያ ለሚገኙ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከኮንታ ዞን እና ኮንታ ኮይሻ ወረዳ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው የፌዴራልና የክልል ምክር ቤት ተወካዮች በተገኙበት በግድቡ አካባቢ የሚገኙ የኮይሻ ወረዳ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ስለተጀመሩት ተግባራት አስመልክቶ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማርቆስ ወንድሙ እንደገለፁት የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመር አካባቢው ያለውን አስደናቂ የተፈጥሮ መልክዓ ምድር እና የተፈጥሮ ሀብት በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ በር ከፍቷል።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ኮረሪማ፣ ቡና እና ቅመማ ቅመም ያሉ የግብርና ምርቶችን በብዛት ለገበያ ለማቅረብ ዕድል በመፍጠሩ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው አንስተዋል።

የአካባቢውን ሁለንተናዊ ልማት ለማፋጠን ለወረዳው ነዋሪዎች የተጀመረው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ በመጠየቅ የተጀመረው ሥራ በስኬት እንዲጠናቀቅ ወረዳው አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአካባቢው መገንባቱ ለዘመናት ተሸፍነው የነበሩ የተፈጥሮ ሀብቶችን የገለጠና በማህበረሰቡ ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ፕሮጀክቱን እንደ ዓይን ብሌን እንደሚጠብቁት አስታውቀው ተቋሙን እየገጠመው ያለውን የመሠረተ ልማት ስርቆት ለመከላከል በዞኑ ውስጥ ጥብቅ ክትትል በማድረግ መሠረተ ልማቱን ለመጠበቅ አስተዳደራቸው ጽኑ አቋም እንዳለው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ መንግስቱ የኮይሻ ከተማንና ዙሪያ ቀበሌዎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ተቋሙ በጀት መድቦ በተቋሙ የራስ ኃይል ኮንስትራክሽን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

እስካሁንም የቁሳቁስ ማጓጓዝ፣ የቅየሳ፣ የጉድጓድ ቁፋሮና የተከላ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመጥቀስ የተጀመረውን ሥራ በዕቅዱ መሰረት ለማጠናቀቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የነዳጅ አቅርቦት እጥረትና በግብዓት አቅራቢዎች በኩል የነበሩ ውስንነቶች ለመዘግየት ምክንያት እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተከሰቱት ችግሮች እልባት እንዲያገኙ በማድረግ የተጀመረው የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ከግብ እንዲደርስ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አቶ አለማየሁ አስረድተዋል።

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው የተቋሙ ዋነኛ ተልዕኮ የኤሌክትሪክ ኃይልን በጅምላ ማቅረብ ቢሆንም ፕሮጀክቶች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ይህ ተግባር ተቋሙ የሕዝብ ሆኖ ለሕዝብ የሚሠራ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ገልፀዋል። የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት መገንባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተቋሙ የሥራ ተቋራጩን በማስተባበርና በጀት በመመደብ እስካሁን የመንገድና የድልድይ፣ የትምህርት ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎች፣ የሆስፒታልና የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታዎችን አከናውኖ ለአገልግሎት ማብቃቱን አቶ ሞገስ አስታውሰዋል።

የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ በኮይሻና ከተማና በዙሪያው እየተከናወነ ያለው የ33 ኪሎ ቮልት (KV) የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በተሻለ ፍጥነት እንዲከናወን ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የምሰሶ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮና የኮንክሪት ምሰሶዎችን የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ ጎን ለጎን ምሰሶዎችን የመትከል ሥራ በከፍተኛ ርብርብ እየተከናወነ ይገኛል።

ኢትዮጵያን ብርሃን የማልበስ ዓላማ ያለው ይህ ግዙፍ ተቋም በኮይሻ አካባቢ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ኃይል ለማቅረብ እየሠራ ያለው ሥራ የዚሁ ትልቅ ዓላማ አካል መሆኑን በማረጋገጥ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል።

Scroll to Top