በሪጅኑ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በተፈጸመ ስርቆት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሷል

በሪጅኑ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በተፈጸመ ስርቆት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሷል

በ2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ በተፈጸመ ስርቆት 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ መድረሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምዕራብ ሪጅን አስታወቀ፡፡

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ በቀለ እንዳስታወቁት በሪጅኑ የሚፈጸሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ ቢመጣም ከነቀምት – ጊዳ አያና ባለ 132 ኪሎ ቮልት እና ከፊንጫ – ሻምቡ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደጋጋሚ ስርቆት እየተፈፀመ ይገኛል።

በሪጅኑ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሰማኒያ ሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት 3 ሺህ 908 የታወር ብረቶች መሰረቃቸውን ገልጸው በዚህም በስርቆት የደረሰው ጉዳት፣ የተሰረቁ ታወሮችን መልሶ ለመጠገን የወጣውን ወጪ እና ኤሌክትሪክ በመቋረጡ የታጠውን ገቢ ጨምሮ 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

በሪጅኑ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ቢሆንም በስርቆት ምክንያት የሚደርሰው የኃይል መቆራረጥ በአካባቢው ባሉ በአምራች ኢንዱስትሪዎች እና በንግድ ተቋማት ላይ የምርት ጥራት መቀነስና መቋረጥ፣ የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል፣ በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በሪጅኑ የሚፈጸሙ ሰርቆቶችን ለመከላከል ከዞን፣ ከወረዳ እና ከቀበሌ የመስተዳደር አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች በአንዳንድ አከባቢዎች ለውጥ ቢያመጡም ችግሮችን በዘላቂነት ማስቆም አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የመሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ የዘረጋው አዲስ አሰራር በመጠቀም በስርቆት የሥጋት ቀጠናዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው በየደረጃው ያሉ የመስተዳድር አካላት የችግሩን ስፋት እንዲረዱና ከተቋሙ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የሪጅኑ የመሰረተ ልማት ጥበቃ ክትትል ባለሙያ ኮሎኔል ተስፋዬ ሱቱማ በበኩላቸው በሪጅኑ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ የስርቆት ዓይነቶች ከተራ ሌብነት ባሻገር በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ሁኔታዎችን ተጠቅመው በቡድን የሚፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሚፈጸሙ ስርቆቶችን ለመከላከልና የመሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ ከሪጅኑ የሥራ ኃላፊዎች እና ከአካባቢው የመስተዳድር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኮሎኔሉ ገለጻ በሪጅኑ የሚሰሩ የቅድመ መከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ስርቆት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን በመጠቆም እጅ ከፍንጅ እንዲያዙና ለህግ እንዲቀርቡ እገዛ እያደረገ ነው።

Scroll to Top