የግል የፋይናንስ ተቋማት በቀጣይ 10 ዓመታት ለሚከናወኑ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ በማድረግ ከተቋሙ ጋር በጋራ እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥሪ አቀረበ።
ተቋሙ ባንኮቹ ለኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ የሚያደርጉበትን ዕድል ለመፍጠር በሀገሪቱ ከሚገኙ የግል ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።


በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደተናገሩት ተቋሙ የተለያዩ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።
ተቋሙ አሁን ላይ ከ900 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያለው ሲሆን የተፈቀደ ካፒታሉ ደግሞ 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር እንደሆነ ገልፀዋል።


የኃይል ዘርፉ እስከ አሁን በኪሳራ ላይ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን የተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ተቋሙ ከዚህ በፊት ከግል ባንኮች ጋር በተናጠል ሲሰራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደመረ ከግል ባንኮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ውይይት ባንኮቹ ስለ ተቋሙ አጠቃላይ ገፅታ ግንዛቤ በመያዝ በቀጣይ በተናጠልና በትብብር ከተቋሙ ጋር በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ እድል ለመፍጠርና ለማመቻቸት ያለመ እንደሆነ አንስተዋል።
ስለሆነም እያደገ ለሚሄደው የኃይል ፍላጎት በአግባቡ ምላሽ ለመስጠት የግል ባንኮች ከተቋሙ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት በመፍጠር በሀገራዊ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፋ ጥሪ አቅርበዋል።
የግል ባንኮች በኢትዮጵያ ብርሃን አሻራቸውን በማሳረፍ ከተቋሙ ጋራ ለቀጣይ 10 ዓመታት አብረው እንዲጓዙም አሳስበዋል።
በዕለቱ የተቋሙ የእስከአሁኑ ጉዞ አጠቃላይ ገፅታ፣ በቀጣይ 10 ዓመታት ዕቅድና የሚያስፈልግ የፋይናንስ መጠን ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

