የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚገነባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሥርቆት ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ለመከላከል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የሲዳማ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አረጋገጡ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋም ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸሙን የክልል መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ እየገመገመ ይገኛል።


የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የመሠረተ ልማት አማካሪ አቶ እንዳሻው እስራኤል በግምገማው ላይ እንደገለጹት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደ ሀገር በመከናወን ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችንና የታቀዱ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት ፋይዳው የጎላ ነው።
በክልሉ እየጨመረ የመጣው የከተሜነት መስፋፋት የሚፈልገውን ኃይል ለማቅረብ ባለፉት አምስት ዓመታት ከተቋሙ ጋር በተሰሩት ሥራዎች በአሁኑ ወቅት በክልሉ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ መደረጉንና በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ሠፊ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውንም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚዘረጉ የጥፋት እጆች በክልሉ ያሉ የልማት ሥራዎች በማስተጓጎል እና የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን በማምከን በተቋምና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ክልሉ በትኩረት መገምገሙን አስረድተዋል።
ስለሆነም ክልሉ የተሻለ ሠላም ያለበት እና ወንጀልን በመከላከል ረገድ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት አማካሪው በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶች ከክልሉ አቅም በላይ ስላልሆኑ አጥፊዎችን እንደማይታገሱና አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወስዱ አረጋገጠዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሠላምና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ አቶ ሸረፋ ለጌሶ በበኩላቸው የማህበረሰብ ለውጥና የሀገር ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው የኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ ሁሉም መሰረተ ልማቶች ሲሟሉና ደህንነታቸው ተጠብቆ አገልግሎት መስጠት ሲችሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ደህንነትን ለማረጋገጥ በርዕሰ መስተዳደሩ ልዩ አማካሪ የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰዋል።
እንደ አማካሪው ገለጻ በክልሉ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ስርቆት በስፋት የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት ሁሉን አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሰራቱ ለውጦች እየታዩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ለውጦችን ለማስቀጠልና በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የመሠረተ ልማቱ ባለቤት እና ባለድርሻ አካላት ስርቆትን መከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን በመደበኛ ዕቅዶቻቸው አካተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የሁለቱ ክልሎች የሥራ ኃላፊዎች ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት በመዘርጋት እና በመከላከል ላይ ያተኮሩ ማህበረሰብ አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶችን በማካሄድ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በቅንጅት እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት።


