ሥልጠናው የፕሮጀክቶችን አካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ስጋቶችን ለመከላከል ያግዛል

ሥልጠናው የፕሮጀክቶችን አካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ስጋቶችን ለመከላከል ያግዛል

በዓለም ባንክ ፋይናንስ በሚደረጉ የፕራይም – 1 ፕሮጀክቶች ላይ ‎በአካባቢያዊ እና ማህበራዊ ስጋት አስተዳደር ዙሪያ የተሰጠው ሥልጠና የአካባቢያዊና ማህበራዊ ስጋቶችን ለመከላከል እንደሚያግዝ የስልጠናው ተሳታፊ ባለሙያዎች ገለጹ።

‎የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የአካባቢ እና ማህበራዊ ስጋት አስተዳደር ቡድን ጋር በመተባበር በባንኩ ፋይናንስ ተደርገው በሚሰሩ ፕሮጀክት ላይ ለሚሰማሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና እና የደቡብ ሱዳን የአካባቢያዊ፣ የማህበራዊ እና የጤና ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል፡፡



‎በተቋሙ የፕራይም – 1 ፕሮጀክቶች የኢንቫሮሜንታል ባለሙያ የሆነችው ወ/ሪት አዝመራ ተስፋዬ እንደገለጸችው ፕሮጀክቶች በሚተገበሩበት ወቅት ከአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ።

‎እነዚህን ችግሮች በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት የቅድመ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱ አስፈላጊ መሆኑን አብራርታለች።

‎ሥልጠናው በዓለም ባንክ አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ስጋት አስተዳደር መስፈርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በተግባር ተደግፎ መሰጠቱ ባለሙያዎቹ የንድፈ ሀሳብ እውቀትን ወደ ተግባር በመለወጥ በፕሮጀክቶቹ ላይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል ግንዛቤ እንዳገኙበትም ተናግራለች፡፡

‌‎በተቋሙ የፕራይም – 1 ፕሮጀክቶች የሙያ ላይ ጤንነትና ደህንነት ባለሙያ አቤል ንጉሴ በበኩሉ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና መስፈርቶች በመተግበር አካባቢያና ማህበራዊ ተጽዕኖ ስጋቶችን መቀነስ ካልተቻለ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከሚሰጠው ጥቅም የበለጠ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁሟል።

‎ ሥልጠናው በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን እንዴት መከላከልና መቆጣጠር እንደሚቻል በቂ እውቀት የፈጠረ መሆኑን ገልጿል፡፡

ሌላኛዋ የሥልጠናው ተሳታፊና በተቋሙ የፕራይም – 1 ፕሮጀክቶች የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያ የሆነችው ወ/ሪት ሕይወት ወርቁ ሥልጠናው በፕሮጀክቶቹ ትግበራ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ስጋት አስተዳደር የባንኩን መስፈርቶች በጠበቀ መልኩ እንዲሆኑ የሚያስችል ግንዛቤ ያገኘችበት መሆኑን ገልጻለች።

‎በተጨማሪም በፕራይም -1 ፕሮጀክቶቹ ዙሪያ በተቋሙ የተከናወኑና በሚመለከታቸው አካላት የጸደቁ የተጽዕኖ ግምገማ ሰነዶችን በመተግበር ውጤት ለማስመዝገብ ሥልጠናው ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ጠቁማለች፡፡

‌‎ባለሙያዎቹ በሥልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ በፕራይም – 1 ፕሮጀክቶች ትግበራ ላይ ውጤት ለማስመዝገብ ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ሥልጠናውን ላጠናቀቁ ባለሙያዎች ሰርተፍኬት ተሰጥቷል።

Scroll to Top