የአዳማ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2017 ግማሽ በጀት ዓመት በቅድመ መከላከል፣ በትንበያ እና የገጠሙ ችግሮችን በማስተካከል ከዕቅዱ በላይ ቢያከናውንም ኃይል በማምረት ረገድ የያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንዳልቻለ አስታወቀ፡፡
የጣቢያ ኃላፊው አቶ መለሰ ሲሎ እንደገለፁት ጣቢያው በግማሽ ዓመቱ በቅድመ መከላከል፣ በትንበያ እና የገጠሙ ችግሮችን በማስተካከል 141 ጥገናዎች ለማከናወን አቅዶ 150 ጥገናዎችን በማከናወን የ106 ነጥብ 21 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል፡፡
በንፋስ ተርባይኖችና በስዊችያርድ 152 የፍተሻ ሥራዎችን ለማከናወን የያዘውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ማሳካቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ይሁንና በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ለማምረት ካቀደው 249 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ውስጥ ማምረት የቻለው 184 ነጥብ 26 ጊጋ ዋት ሠዓት ብቻ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ የኃይል ማምረት አፈፃፀሙ ከዕቅዱ አንፃር ዝቅ ያለ ቢሆንም የንፋስ ተርባይኖች የሚቆሙበትን ጊዜ በመቀነስ እና አስተማማኝ የጥገና ሥራዎችን በመስራት በተለዋዋጭ የንፋስ ሁኔታዎች ውስጥ ያልተቋረጠ ኃይል ማምረት ተችሏል፡፡
የጣቢያው የጥገና ባለሙያዎች ቴክኖሎጂን በቀላሉ መላመዳቸውና የሥራ ተነሳሽነታቸው ከፍ ያለ መሆኑ ለበጥገና ሥራ ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
የተቋም ሀብት ዕቅድ ሶፍትዌር ወይም ERP፣ የሳፕ ጥገና ሞጁልና የኃይል አስተዳደር ሥርዓቶች እና ሌሎች የለውጥ መሳሪያዎች በጣቢያው መተግበራቸው ለጣቢያው የኦፕሬሽን ሥራዎች ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ገልፀዋል፡፡
ኃላፊው እንደተናገሩት የጥገና ሥራዎች በዕቅድ መተግበራቸው የሥራ ጊዜን ውጤታማ በማድረግ እና የመሳሪያዎችን የህይወት ዘመን በማራዘም በጣቢያው የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖር አስችሏል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





