በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ እየተተገበሩ ያሉ አሰራሮች ሕጋዊ ሂደትን ተከትለው መከናወናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ሥራ አስፈጻሚ አሳሰቡ።
ሥራ አስፈጻሚው አቶ ዱጉማ ነዳ ከተቋሙ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
ውይይቱ ዓላማ በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎች ከመደገፍ ባለፈ የተቋሙን የፋይናንስ አቅም በእጅጉ እየተፈታተኑ ባሉት የታወር ስርቆትና የካሳ ክፍያ ጉዳዮች ዙሪያ መምሪያው በምን አግባብ እየሰራ ነው የሚለውን አይቶ ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
ለውይይት መነሻ እንዲሆን አምስት አባላት ያሉት የጥናት ኮሚቴ በማቋቋም በመምሪያው እና በስሩ ባሉ ክፍሎች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦች ለማመላከት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት መሰራቱን ተናግረዋል።
መምሪያው ቅንጅታዊ አሰራርንና ሙያዊ ብቃትን በማሳደግና አሰራሮች ሕግን የተከተሉ መሆናቸውን በመቆጣጠር ተቋሙን በመጠበቅና በመከላከል በኩል ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ በሀገር ደረጃ የሚሰራቸውን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ከብክነት በፀዳ መልኩ በውጤታማነት ለመፈፀም የመምሪያው ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በሕግ አገልግሎት መምሪያና በሥሩ በሚገኙ የሥራ ክፍሎችን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመለየት እና የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማመላከት የተሰራው የዳሰሳ ጥናትም ለውይይቱ ተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡
በመምሪያው ውስጥ ከሠራተኛ አቅም ግንባታ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመፈጸም አቅምና ከግብዓት አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮች እንዲሁም ከሌሎች የተቋሙ የሥራ ክፍሎች ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በጥናቱ ተዳሷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ጥናቱ ራሳቸውን እንዲያዩና በሥራ ክፍሎች መካከል እርስ በእርስ የመማማር ዕድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
መምሪያው ተቋሙን የሚመጥን ሥራ ለመስራት ያስችለው ዘንድ ሊፈቱና ሊታዩ ይገባሉ ያሏቸውን ሀሳቦችና አስተያየቶች አንስተው መሰል ጥናቶችና ወይይቶች በየጊዜው የሚደረጉበት አሠራር እንዲዘረጋም ጠይቀዋል፡፡
የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም በቀለ በበኩላቸው ከተሳታፊዎች የተነሱ እንዲሁም በጥናቱ የተለዩ ችግሮችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በተቋማዊ ለውጡ የሕግ ክፍል ሊኖረው የሚችለውን ሚና እንዲወጣ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከታወር ስርቆትና ከካሳ ክፍያ ጋር ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች፣ ከፍትህና አስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡
የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ በፍርድ ቤት ባሉ ጉዳዮች ዙሪያም መረጃና ማስረጃ በማጠናከር የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅና ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት ዳይሬክተሯ ተቋማዊ አሰራሮችን በመፈተሸ በሕግ እንዲደገፉ ብሎም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን መምሪያው በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





