የተቋሙ ሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አከበሩ

የተቋሙ ሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አከበሩ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሴት ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች በዓለም ለ114ኛ በሀገር አቀፍ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ « ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ» በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብረዋል፡፡

በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደተናገሩት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር ሴቶች በሁሉም ዘርፍ አቅማቸውን በማጎልበት ውጤታማ እንዲሆኑ የተጀመረውን ጥረት በማስቀጠል ሊሆን ይገባል፡፡

የሥራ ቦታዎችን  ከጾታ መድልዖ የጸዱ፣ አካታች እና አሳታፊ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረትም የተቋሙ ሴት ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በተቋሙ  የሴቶች እና ማህበራዊ መመሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ በበኩላቸው ሴቶች  የሚያገኙትን ዕድል ሳያባክኑ አሟጠው  በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ የድጋፍ እርምጃዎችን ያመቻቻ ቢሆንም ዕድሉን ከመጠቀም አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ስለሆነም ተቋሙ ለሴት ሠራተኞች ያስቀመጣቸውን የድጋፍ እርምጃዎች በአግባቡ በመጠቀም የሚጠበቅባቸውን ተቋማዊና ሀገራዊ አስተዋጽኦ ማበርከት አንዳለባቸውም ገልፀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ በጡት እና በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና  እና  ሥነ ግጥም ቀርቧል፡፡

በተመሳሳይ በዓሉ በተቋሙ በአዳማ 1 እና 2፣ በቆቃ፣ በአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እንዲሁም በደሴና በማዕከላዊ ሪጅን 2 በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top