“ጣቢያው የአንድ ትውልድ ጥያቄን የመለሰ ነው” ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

“ጣቢያው የአንድ ትውልድ ጥያቄን የመለሰ ነው” ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

የወራቤ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን መገንባቱ የአንድ ትውልድ ዘመን ጥያቄን መመለስ መቻሉን የኢፌዲሪ  የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ገለፁ።

ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በማከፋፈያ ጣቢያው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ የስልጤ ዞንን ቀጣይ የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥንና የአካባቢውን እምቅ አቅም ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልፀዋል።

የኃይል መሰረተ ልማቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የልማት ፍላጎት ከማርካት ባለፈ የወራቤ ከተማንና አጠቃላይ የስልጤ ዞንን የንግድና የኢኮኖሚ መናኸሪያ ለማድረግ ለተያዘው ግብ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት።

የወራቤ ከተማ በንግድና በማህበራዊ ትስስር ረገድ ያላትን ስልታዊ ጠቀሜታ ያነሱት ወ/ሮ ሙፈሪያት ከተማዋ በርካታ መጋቢ መንገዶች የሚገናኙባትና ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተናገድባት በመሆኗ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ማግኘቷ ስትራቴጂካዊ አቅሟን ይበልጥ እንደሚያጎለብተው ጠቅሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሀገር ደረጃ የተከናወኑ የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች የሀገሪቱን ከፍታ ያበሰሩ ብቻም ሳይሆኑ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኃይል ሚዛንን ያስተካከሉ ትልልቅ ስኬቶች መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ ጣቢያው የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክርና የሚያቀናጅ ታሪካዊ መሰረት ነው።

በአሁኑ ወቅት የኃይል አቅርቦቱ አስተማማኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስልጤ ዞን በግሉ ዘርፍና በመንግሥት ትብብር ወደ አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመሩ የኢንዱስትሪ ልማቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀን ከሌሊት በቁርጠኝነት የሠሩትን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር፣ የሥራ ተቋራጭና አማካሪ አካላትን ያደነቁት ሚኒስትሯ የአካባቢው አመራርና ማህበረሰብም ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ስሜት በመንከባከብ ላሳዩት ቀና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ይህ የተቀናጀ የሥራ ባህልና የባለቤትነት መንፈስ ለሌሎች መሰል ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችም በምሳሌነት ሊወሰድ የሚገባው ታላቅ ተሞክሮ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top