“የኤሌክትሪክ ኃይል የብልፅግና ምሰሶ ነው” ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

“የኤሌክትሪክ ኃይል የብልፅግና ምሰሶ ነው” ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገለፁ።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የወራቤ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የጣቢያው መገንባት ተቋሙ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በመላ ሀገሪቱ ለማዳረስ ለያዘው ስትራቴጂካዊ ግብ ስኬት ትልቅ ማሳያ ነው።

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ለአገልግሎት መብቃት ለአካባቢው ቀጣይ የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ትልቅ መደላደል እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት።

የጣቢያው ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በይፋ ለማብሰር የተዘጋጀው የምርቃት መርሃ ግብር የተገኘውን ስኬትና ደስታ ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ለመካፈል መሆኑን አስረድተዋል።

ተቋሙ በመላ ሀገሪቱ በርካታ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን እየገነባ እንደሚገኝ የገለፁት ኢንጂነር አሸብር ዘንድሮ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃቱን አብራርተዋል።

እነዚህ ግዙፍ የኃይል መሠረተ ልማቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማደጉንም ነው የገለፁት።

የወራቤ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የስልጤ ዞንና የወራቤ ከተማ አመራሮች እንዲሁም ማህበረሰቡ ላደረጉት ልዩና አርአያነት ያለው ድጋፍ በተቋሙ ስም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚልን ጨምሮ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top