የኃይል ማመንጫ ግድቦች በጥሩ የደህንነት ቁመና ላይ ይገኛሉ

የኃይል ማመንጫ ግድቦች በጥሩ የደህንነት ቁመና ላይ ይገኛሉ

የኃይል ማመንጫ ግድቦች በአስተማማኝ እና በጥሩ የደህንነት ቁመና ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በተቋሙ ጀኔሬሽን ቢዝነስ የግድብ ደህንነት ክትትል እና ቁጥጥር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤሊያስ ደላሽ እንዳስታወቁት የግድቦችን ደህንነት ለማረጋገጥና ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች አስቀድሞ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ በግድቦችና ተያዥ አካላት ላይ በየጊዜው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ይከናወናል፡፡



በዚህም ባለፉት አስር ወራት በመበልካ ዋከና፣ በግልገል ጊቤ አንድና ሁለት፣ ጊቤ ሶስት፣ ጢስ አባይ፣ ጣና በለስ፣ ቆቃ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ተከዜ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና በኮይሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ፕሮጀክት ግድብ እና ተያያዥ ህዳጎች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

የግድቦች ጥናት፣ ዲዛይን፣ ግንባታ፣ የቁጥጥር፣ የፍተሻ፣ ሥራ የማስጀመርና በየጊዜው የሚከናወኑ የግድብ ደህንነት ክትትል ሥራዎች  ዓለም አቀፍ አሰራሮችንና ተሞክሮዎችን መሰረት በማድረግ እንደሚከናወኑ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት ተቋሙ የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን ለማከናወን ዓለም አቀፍ የግድቦች ኮሚሽን (ICOLD)፣ የምስራቅ አባይ ተፋሰስ የቴክኒክ ትብብር ቢሮ / የዓባይ ተፋሰስ አነሳሽነት (ENTRO/NBI)፣ የህንድ የግድቦችና ተያያዥ መዋቅሮች ምርመራና ጥገና፣ የአሜሪካ ጦር ሰራዊት ኢንጂነሮች ኮርፖሬሽን፣ የአውሮፓ የግድብ ክትትል ደረጃዎች እና የመሳሰሉ መመሪያዎችን እንደሚጠቀም አብራርተዋል፡፡

የግድብ ክትትል ሥራ የግድቡን ደህንነት፣ የአሰራር ቅልጥፍናን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃንና በታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚከናወን ያነሱት አቶ ኤሊያስ ሥራው የውሃውን ግፊት፣ የመዋቅሩን መረጋጋት እና በግድብ አካላት ላይ ሊታዩ የሚችሉ አነስተኛ ለውጦችን ጭምር በጥንቃቄ መከታተልን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡

ይህም በግድቦቹ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ስንጥቆችን እና የውሃ መፍሰስ ወይም የመሬት መንሸራተት ምልክቶችን በቅድሚያ በመለየት አስከፊ አደጋዎች ሳይከሰቱ የመከላከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያስችላል ነው ያሉት።

ባለፉት አስር ወራት ውስጥ በተከናወኑ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራዎች የኃይል ማመንጫ ጣቢያና ፕሮጀክት ግድቦች እና ተያያዥ መዋቅሮች በአስተማማኝ እና በጥሩ የደህንነት ቁመና ላይ እንደሚገኙ አቶ ኤሊያስ አረጋግጠዋል፡፡

በየጊዜው በተደረገው የክትትል ሥራ ግድቦቹን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ምንም አይነት ስጋት አለመገኘቱንና ይህም ግድቦቹ ያለምንም ስጋት በአስተማማኝ መልኩ ኃይል እንዲያመነጩ በማድረግ የኦፕሬሽን ሥራው በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲቀጥል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡

የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ በየጊዜው በግድቦች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማወቅ ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚከናወን ቢሆንም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክትትል የተሰበሰቡ መረጃዎች እና የተከናወኑ ተግባራት በወደፊት ለሚከናወኑ ተመሳሳይ ሥራዎች በግብዓትነት እንደሚያገለግሉ ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡

በተቋሙ ባለሙያዎች እየተከናወነ ካለው የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ በተጨማሪ በቀጣይ የኃይል ማመንጫ ግድቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉበትን ሁኔታ ለማስጠናት የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን አቶ ኤሊያስ አስታውቀዋል፡፡

Scroll to Top