የአጋሮ ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ ሙሉ አቅም እንዳለው ተገለፀ

የአጋሮ ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ ሙሉ አቅም እንዳለው ተገለፀ

የአጋሮ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በአካባቢው በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝ ሁኔታ በማሟላት ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ ሙሉ አቅም ያለው መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ አስታወቁ

የጣቢያው ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ሞሲሳ እንደገለጹት ማከፋፈያ ጣቢያው በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የነበረው የኃይል መጠን 132 ኪሎ ቮልት ብቻ ነበር።

በወቅቱም በአንድ ባለ 16 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመር እና በሦስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አማካኝነት ለአጋሮ ከተማና ለአካባቢው ውስን ማህበረሰብ ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርብ እንደነበር አስታውሰዋል።  ይሁን እንጂ በአካባቢው በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ተከትሎ በ2008 ዓ.ም ሰፊ የአቅም ማሳደግና የማስፋፊያ ሥራዎች ተከናውነውለታል።

በተከናወነው በዚህ የማስፋፊያ ሥራ የጣቢያው የቮልቴጅ መጠን ከነበረበት 132 ወደ 230 ኪሎ ቮልት ከማደጉም በላይ ተጨማሪ አንድ ባለ 20 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመርና ሦስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እንዲኖሩት ተደርጓል። ይህ እርምጃ የጣቢያውን የኃይል አቅርቦት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ካሳደገው ባለፈ ተደራሽነቱን በስፋት ለመጨመር ማስቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ጣቢያው ከጅማ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ በባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር ኃይል የሚቀበል ሲሆን በስድስት ባለ 15 እና 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አማካኝነት ለአጋሮ፣ ጌምቤ፣ ደንቢ፣ ጋትራ፣ ጌራ፣ ቶባ፣ በሻሻ እና ስግሞ ከተሞችና ወረዳዎች ጭምር በ100 ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ውስጥ ለሚገኙ አካባቢዎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እያሰራጨ ይገኛል።

በተጨማሪም ጣቢያው ከበደሌ ማከፋፈያ ጣቢያ በሚመጣው የ230 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ ኃይል በቀጥታ የመስጠትና የመቀበል (LILO) የቴክኒክ አቅም እንዳለው አቶ ዮሴፍ አብራርተዋል።

በጣቢያው የሚገኙት ሁለቱ ትራንስፎርመሮች በአጠቃላይ መሸከም ከሚችሉት 36 ሜጋ ቮልት አምፔር ወይም 29 ሜጋ ዋት የኃይል መጠን ውስጥ በአሁኑ ወቅት ለደንበኞች እየቀረበ ያለው 50 በመቶው ብቻ እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ይህ አኃዝ ጣቢያው ወደፊት አዳዲስ የኃይል ፍላጎት ለሚያቀርቡ ተጨማሪ ደንበኞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመስጠት የሚያስችል በቂና ዝግጁ የሆነ ትርፍ አቅም እንዳለው የሚያሳይ ነው።

ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ከዕለት ተዕለት የኦፕሬሽን ሥራዎች ጎን ለጎን የሚያጋጥሙ የአቅርቦት መስተጓጎሎችን በወቅቱ ለመፍታትና የጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

የኦፕሬሽን ሥራውን ይበልጥ ለማቀላጠፍና ዘመናዊ ለማድረግም የ33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮችን የመቆጣጠሪያ ብሬከር ወደ ዘመናዊው የጂአይኤስ (GIS) ቴክኖሎጂ የመቀየር ሥራ ተጀምሯል።

በአሁኑ ወቅት የዚህ ፕሮጀክት የሲቪል ግንባታ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል። ይህ የማዘመን ሥራ ከብሬከር አቅም ማነስ ጋር ተያይዘው ይከሰቱ የነበሩ የቴክኒክ ችግሮችን በዘላቂነት ከመቅረፉም በላይ አሁን ያሉትን የ33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ቁጥር ከሦስት ወደ ስምንት በማሳደግ በርካታ ተጨማሪ ደንበኞችን በቅልጥፍና እና በታማኝነት ማስተናገድ የሚያስችል ሰፊ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል።

Scroll to Top