ማመንጫ ጣቢያው የ9 ወራት ዕቅዱን 99 ነጥብ 1 በመቶ አሳካ

ማመንጫ ጣቢያው የ9 ወራት ዕቅዱን 99 ነጥብ 1 በመቶ አሳካ

የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 256 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማምረት የዕቅዱን 99 ነጥብ 1 በመቶ ማሳካቱን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ::

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሙሉቀን ተሰማ እንዳስታወቁት ጣቢያው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ32 ተርባይኖች 258 ነጥብ 28 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማመንጨት አቅዶ 256 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማምረት ችሏል።

አፈፃፀሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ8 ጊጋ ዋት ሰዓት ወይም የ3 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ገልፀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጣቢያው ዝግጁነት ወይም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ (Plant Availability) እና ኃይል ከሚያመነጨው አቅም አንፃር ጥቅም ላይ የዋለው (Utilization Index – UI) አፈፃፀም ከዕቅዱ በላይ መሆኑን አብራርተዋል።

“አንድም የንፋስ ተርባይን ያለ ሥራ እንዳይቆም” የሚለውን መርህ በቁርጠኝነት መተግበር መቻሉና የሠራተኞች የጋራ ቅንጅት ማደግ ለተመዘገበው‎አፈፃፀም ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

ከዋናው የኃይል ማመንጨት ተግባር ጎን ለጎን በፕሮጀክቱ የውል ስምምነት ወቅት ያልተካተቱና የተጓደሉ አስፈላጊ ዕቃዎችን በመለየት ድጋሚ ለጣቢያው እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ ‎ሲከናወን መቆየቱንም ነው የገለፁት፡፡

ከጣቢያው የኦፕሬሽን ሠራተኞች መኖሪያ ቤት አቅርቦት ጋር ተያይዘው የነበሩ ቅሬታዎች 90 በመቶ መፈታታቸውንም ነው አቶ ሙሉቀን የጠቀሱት፡፡

ይሁን እንጂ በጣቢያው ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለማሟላት ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመው ግንባታውንም ለማከናወን ከፕሮጀክት ቢሮው ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጣቢያው የነዳጅ ማደያ ታንከር ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝና የጥበቃ ማማዎችን ለመገንባትም አስፈላጊው እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

የጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራዎች ይበልጥ ለማቀላጠፍ በስካዳ (SCADA) እና አውቶሜሽን የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ገልፀው ይህንን ለማሳካትም ከፕሮጀክት ቢሮውና ከሥራ ተቋራጩ ጋር በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዘበዋል።

Scroll to Top