ጣቢያው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን እየሰራ ነው

ጣቢያው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን እየሰራ ነው

የመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ እንደገለጹት ጣቢያው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በጣቢያው ዙሪያ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ላይ የውሃ ጉድጓዶችን በማስቆፈር ማህበረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ኢብሳ ጤና ጣቢያን ሰርቶ ማስረከቡን ገልጸዋል።

በኃይል ማመንጫ ጣቢያው ዙሪያ የሚገኙ 12 ቀበሌዎችን ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት የመብራት ተጠቃሚ መደረጋቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ቀሪ አካባቢዎችን ተጨማሪ 330 ሚሊዮን ብር በመመደብ የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ ሮቤ ጌርጀዳን ከጌዴዶ ከተማ የሚያገናኝ 10 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ጣቢያው መስራቱንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከጣቢያው እስከ በቆጂ መገንጠያ ያለውን 26 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እና ከጣቢያው እስከ አዳባ ያለውን 30 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ የጥገና ሥራ ለመስራት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በጣቢያው ግቢ የሠራተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች የሚማሩባቸው ከኬጂ እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ 250 ለሚሆኑ የቅድመ መደበኛ የአካባቢው ተማሪዎችም የትራንስፖርት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

የዋቤ ኢብሳ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አማና ፈቶ እንደገለጹት ጣቢያው ውሃ፣ መብራት እና የትምህርት ቁሳቁስ ለትምህርት ቤቱ እያቀረበ ነው።

ይህም ልጆቹ ርቀው ሳይሄዱ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የአካባቢው አባገዳ የሆኑት ሐጂ እንድሪስ ሐጂ ጉራሪ በበኩላቸው ጣቢያው ለአካባቢው ማህበረሰብ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያና መንገድ ከመስራት ባለፈ የውሃና የመብራት ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም የአካባቢው ማህበረሰብ ርቆ ሳይሄድ ንጹህ የመጠጥ ውኃ እንዲያገኝ፣ ልጆቹን እንዲያስተምርና የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የኃይል ማመንጫ ጣቢያው እያከናወነ ላለው የልማት ስራ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አስተያየት ሰጪዎቹ በዚህም ማህበረሰቡ በጣቢያው ላይ ያለው የእኔነት ስሜት እያደገ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም ከጣቢያው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የጣቢያውን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የመልካ ዋከና ውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ የጀመረው በ1980 ዓ.ም ሚያዚያ 15 ቀን ነው።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top