የአዳማ ከተማ አስተዳደር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የመጠበቅ ግዴታውን እንደሚወጣ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ጋር በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ ስለሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሸን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለከንቲባው እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀሙ የሚገኙ የስርቆት ወንጀሎች እየጨመሩ መጥተዋል።
ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት በስርቆትና የተሰረቁ የኃይል መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከአንድ ቢሊየን ብር የሚበልጥ ጉዳት እንደደረሰበት ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ቀበሌዎች እየተስፋፋ የመጣውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ለመከላከል የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም መዋቅሮቹ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
በተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንዳስታወቁት በአዋሽ መልካሳ-ወለንጪቲ በተዘረጋው መስመር ኡላጋ ቀበሌ ላይ 3 ምሰሶዎች በስርቆት የተነሳ በመውደቃቸው እስካሁን የጥገና ሥራ ማከናወን አልተቻለም።
ተቋሙ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራት በኩል መልካም ጅምሮች እንዳሉት የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ ይሁን እንጂ በወንጀል ፈፃሚዎቹ ላይ የሚጣለው ቅጣት ጠንካራና አስተማሪ አለመሆኑን አንስተዋል።


የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በሰጡት ምላሽ ከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት እየጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ ግዴታው መሆኑን ይረዳል።
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ስርቆት ለመከላከል በሚከናወነው ሥራ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው እንደሚከታተሉትና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች መመሪያ እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡
ከኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት ስርቆት ባሻገር በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ሥር የሚከናወኑ ግንባታዎችን በመከላከል የህብረተሰቡን እና የመስመሩን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ ለመስራት መታቀዱንም ከንቲባው ገልፀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ሊሰራቸው ላሰባቸው ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ኃይል ተቋሙ ታሳቢ አድርጎ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric ;
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com:/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም