በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግልገል ጊቤ 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለሠራተኞቹ ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን የጣቢያው አስተዳደር፣ ንብረትና አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ታምራት ቸኮል እንደተናገሩት የማመንጫ ጣቢያው ሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢ ተፈጥሮላቸው ሥራቸውን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያከናውኑ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ለሠራተኛው የክበብ አገልግሎት፣ የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው የመዋኛ ገንዳ፣ የዲ ኤስ ቲቪ እና ሌሎች የመዝናኛ አማራጮች መመቻቸቱን ተናግረዋል።
ከኃይል ማመንጫ ቤቱ እስከ ሠራተኛ መኖሪያ ያለው 13 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠመዝማዛና በተለይ በክረምት ወራት ናዳ የሚበዛበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ታምራት ማሽኖችን ከሌላ ቦታ በማስመጣት የመንገድ ጠረጋ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በመንገዱ አስቸጋሪነት ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ መኪኖች በሽፍት የሚተላለፉበት አሰራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
የማመንጫ ጣቢያው ከከተማ የራቀ በመሆኑ ጣቢያው የትራንስፖርት አገልግሎት በመመደብ ሠራተኛው የሚያስፈልገውን ነገር የሚሸምትበት በሳምንት ሁለት የገበያ ቀን ማመቻቸቱንም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ታምራት ገለፃ የጣቢያውን ሠራተኞች አቅም ለማጎልበት አጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠና ከመስጠት በተጓዳኝ ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በኮምፒዩተርና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት መስክ መምህራን ማመንጫ ጣቢያው ድረስ መጥተው እንዲያስተምሩ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ጣቢያው የመምህራንን ማረፊያ፣ የመመላለሻ ትራንስፖርት፣ የመማሪያ ክፍል እና በኃይል ማመንጫ ቤቱና በማከፋፊያ ጣቢያው በተግባር የታገዘ ትምህርት የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን ገልጸዋል።
ጣቢያው ባመቻቸው የትምህርት ዕድል ቀደም ሲል 38 ሠራተኞች የተመረቁ ሲሆን 40 የሚሆኑት ደግሞ በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም ከወልቂጤ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ጋር በመተባበር 20 የሚደርሱ የጣቢያው ሠራተኞች ከደረጃ 1 እስከ 4 ተምረው መመረቃቸውንም ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።
ይህም ሠራተኞች ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲሠሩና ሙያዊ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ የሠራተኛውን ምቾት በመጠበቅ በሥራ ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ የመኖሪያ ካምፕ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
የግልገል ጊቤ 2 የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 219 ሠራተኞች አሉት።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





