ጣቢያው በሩብ ዓመቱ ከ102 ጊጋ ዋት ስዓት በላይ ኃይል አምርቷል

ጣቢያው በሩብ ዓመቱ ከ102 ጊጋ ዋት ስዓት በላይ ኃይል አምርቷል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 102 ነጥብ 3 ጊጋ ዋት ሠዓት ማምረቱን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ እንደገለጹት ጣቢያው በሩብ ዓመቱ 120 ነጥብ 6 ጊጋ ዋት ስዓት ለማምረት አቅዶ 102 ነጥብ 386 ጊጋ ዋት ሠዓት ኃይል በማምረት የዕቅዱን 84 ነጥብ 84 በመቶ ነው።

በ2016 በጀት ዓመት የመጨረሻ ወራት በጣቢያው ግድብ ላይ የነበረው ውሃ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ በግድቡ የተሻለ ውሃ ለመያዝ ሲባል በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ጣቢያው በአንድ ዩኒት ብቻ እንዲሰራ በመደረጉ አፈፃፀሙ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ግድቡ በቂ ውኃ በመያዙ እና በጣቢያው ላይ የቅድመ መከላከል፤ የትንበያና የሁኔታ አመላካች ጥገና ሥራዎች በእቅድ ተይዘው እየተከናወኑ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያት የተሻለ ኃይል ለማምረት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ጣቢያው ያለምንም መልሶ ግንባታ ከ36 ዓመት በላይ በማገልገሉ በኦፕሬሽን ሥራው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንና የተርባይኖቹን ኃይል የማምረት አቅም ከ38 ነጥብ 25 ሜጋ ዋት ወደ 30 ሜጋ ዋት ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።

ጣቢያው ካሉት አራት ተርባይኖች አንዱ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በመለዋወጫ ዕቃ ምክንያት አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑንም አንስተዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት በጣቢያው ከሚሰሩ የጥገና ሥራዎች በተጓዳኝ በጣቢያው ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ ለመስራት የሩሲያ ባለሙያዎች በቀጣይ ሳምንት ወደ ሀገር ቤት ገብተው ጣቢያውን ካዩ በኋላ ስምምነቱ ተፈርሞ ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህም የኦፕሬሽን ሥራውን በማሻሻል ጣቢያው በሙሉ አቅሙ ኃይል ወደ ማምረት እንዲገባ ያስችለዋል ብለዋል።

ጣቢያው በ2016 በጀት ዓመት 434 ጊጋ ዋት ስዓት ለማምረት አቅዶ 603.187 ጊጋ ዋት ስዓት በማምረት የእቅዱን 138 ነጥብ 98 በመቶ ማሳካቱ ይታወሳል።

በ1980 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የመልካ ዋከና የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአራት ተርባይን 153 ሜጋ ዋት የማምረት አቅም አለው።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top