የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮችና ሠራተኞች በተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት የደም ልገሳ ዛሬ አካሂደዋል፡፡
የደም ልገሳ መርሃግብሩ በተለያዩ ምክንያቶች ደም ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲውል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው የተቋሙ የፋይናንስ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደገለፁት በተቋሙ ዋና መ/ቤት የደም ልገሳ ፕሮግራም መዘጋጀቱ የሠራተኛው የሥራ ሰዓት ከመቆጠቡም በላይ ደም ለመስጠት ፈልገው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ ደም እና ህብረህዋስ አገልግሎት ለመሄድ ያልቻሉትን ሠራተኞች በቅርበት ለማግኘት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በተቋሙ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሐ ጌታቸው በበኩላቸው ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ግንዛቤያቸውን በማሳደግ የደም ባንክ አባል ሆኖ ደም በመለገስ ህይወትን የመታደግ በጎ ተግባርን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል፡፡
ደም ለመጀመሪያ ግዜ ሲለግሱ ያገኘናቸው አቶ ካሰሁን ጸሀይ፣አቶ አብደላ ሻንቆ እና አቶ ታምሩ ባቱ ቢያንስ የሶስት ሰው ህይወት ሊታደግ የሚችል ደም ደ መለገስ በመቻላቸው እንደተደሰቱ እና ተቋሙ ይህን በማመቻቸቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም መሰል የደም ልገሳዎች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ሙሉቀን ዮሴፍ እና ወ/ሮ ፋናዩ ዘበነ በበኩላቸው ደም ልገሳውን ለመጀመሪያ ግዜ ቢሰጡም የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ጉዳት ደርሶባቸው ህይወታቸው ከማያውቁት ሰው በተለገሰ ደም በመትረፉ ደም ለመስጠት መወሰናቸውን ገልፀዋል፡፡
አቶ ያለውአይቀር ማንደፍሮ እና አቶ ኤርሚያስ ጥላሁን እንደተናገሩት ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ደም መለገሳቸውን አውስተው ደም መሥጠት ዘር፣ጎሳ እና ጾታ ሳይለይ ህይወቱን ሊያጣ የነበረን ሰው ህይወቱን መመለስ ከስጦታዎች በላይ ስጦታ እና የበጎ ተግባርም ምሳሌ እንደሆነ መረዳታቸውን ተናግረዋል ፡፡
ከ 1984 ዓ.ም. ጀምሮ ለ 118 ጊዜያት ደም የለገሱት በደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የትምህርት እና የቅስቀሳ ባለሙያ የሆኑት ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ እንደተናገሩት ደም መለገስ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትል እና ዘረፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮችና ሠራተኞች በደም እጥረት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ የበርካታ ወገኖቻቸውን ህይወት መታደግ እንደሚቻል በመረዳት በዚህ በጎ ተግባር ላይ በመሳተፋቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብላዋል፡፡
ደም የሚሞት እና የሚያረጅ እንዲሁም ራሱን የሚተካ በመሆኑ ክቡሩን የሰው ህይወት ልናድንበት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተቋሙ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሼን መምሪያ ይህን ፕሮገራሙ አስተባብሮ ማዘጋጀቱ የሚመሰገን ተግባር እንደሆነ ያወሱት ሲስተር አሰጋሽ በልገሳ መርሃግብሩ 27 ዩኒት ደም መለገሱንና በቀጣይም በተሻለ እንደሚሰበሰብ ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል ፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



