በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግልገል ጊቤ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክትን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የሳይቱ ሱፐርቫይዘር ገለጹ።
ሱፐርቫይዘሩ አቶ ሙሐመድ አሕመድ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የ250 መኖሪያ ቤቶች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ክሊኒክ፣ ቢሮዎችና የሁለት ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እንዲሁም 6 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ያካተተ ነው።
በአሁኑ ወቅት 200 መኖሪያ ቤቶች በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ከእነዚህ ውስጥ 175 ቤቶች ቆርቆሮ መልበሳቸውን የጠቆሙት ሱፐርቫይዘሩ የሁለቱ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታው በመፋጠን ላይ መሆኑን በመጥቀስ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 44 ነጥብ 64 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
የግልገል ጊቤ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሥራ ጥራቱን ጠብቆ መሉ በሙሉ እስከ ዓመቱ መጨረሻ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
የግንባታ ሥራውን የሚያከናውነው ዓይናለም ጋሻው ሕንጻ ሥራ ተቋራጭ የሳይቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ፈንታ በበኩላቸው ግንባታውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ባይቻልም ከተቋሙ ጋር በትብብር በመስራት በዚህ ወር መጨረሻ የ150 ቤቶች የማጠናቀቂያ ሥራ ለመፈፀም እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ግንባታቸው ያልተጀመሩ 50 ቤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ከዚህ ወስጥ የ18 ቤቶች ግንባታ በሚቀጥሉት ሳምንታት ይጀመራሉ ነው ያሉት።
የሲሚንቶ እጥረት፣ ወቅታዊው የዋጋ ንረት እና በአካባቢው ብቁ የሠው ኃይል ያለመኖር ፕሮጀክቱን እየፈተኑት መሆኑን ገልጸዋል።
የጣቢያው አስተዳደር፣ ንብረትና አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ቸኮል በበኩላቸው የመኖሪያ ቤቱ መገንባት ለሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠር ሥራቸውን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያከናውኑ የሚረዳ ነው ብለዋል።
አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ከከተማ ርቆ የሚገኝና የልጆች መማሪያ ትምህርት ቤት የሌለው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ታምራት የአዲሱ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ችግሮቹን በዘላቂነት በመፍታት ሠራተኛው ልጆቹንና ቤተሰቡን ይዞ ተረጋግቶ ለመኖር 㙀ንደሚያስችለው ተናግረዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ መንገዱ ጠመዝማዛና ናዳ የበዛበት በመሆኑ ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ላይ ተግዳሮት ፈጥሮ ቆይቷል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



