የጎዴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዳንጎቴ ግሩፕ አማካኝነት ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ጌዲዮን አበራ እንደገለፁት የጎዴ ማከፋፈያ ጣቢያ ከራይቱ በባለ 230 ኪሎ ቮልት ኃይል የሚያገኝበት አንድ ገቢ መስመር እንዲሁም በ132 እና 33 ኪሎ ቮልት ለተለያዩ አካባቢዎች ኃይል የሚሰጥበት ሰባት ወጪ
መስመሮች አሉት።
ጣቢያው በ132 ኪሎ ቮልት ለቀብሪደሃር ማከፋፈያ ጣቢያ፣ በ33 ኪሎ ቮልት ለጎዴ፣ ሀዳዋይ እና አዳዲሌይ ከተሞች እና በዙሪያው ለሚገኙ አካባቢዎች እንዲሁም ለሁለት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


አሁን እያቀረበ ካለው በተጨማሪ አዲስ ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል 25 ሜጋ ቮልት አምፔር የመጫን አቅም ያለው አንድ ትራንፎርመር መተከሉንና የማስፋፊያ ሥራው መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የማከፋፈያ ጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራ ለማዘመን የሚያስችል የጂ አይ ኤስ ብሬከር ቅየራ ሥራ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
የማስፋፊያ ግንባታው በሪጅኑ አቅም በመከናወኑ አዳዲስ መሐንዲሶች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች የልምድና የዕውቀት ሽግግር እንዲያገኙ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ጣቢያው ካለው የመጫን አቅም አንጻር ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎች ቢመጡ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።



