በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል እና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰጣቸውን አደራ በኃላፊነት እንደሚወጡ በሪጅኖች የተመደቡ የፊዚካል ሴኩሪቲ ከፍተኛ መኮንኖች አረጋገጡ።



ከፍተኛ መኮንኖች በተቋሙ ንብረቶች ላይ የሚፈጸሙ ጉዳቶችን በመከላከል ረገድ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያከናወኗቸውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተቋሙን ንብረቶች በመጠበቅ እና የሚፈጸሙ ስርቆቶችን በመከላከል እንዲሁም ስርቆት የሚበዛባቸውን የስጋት ቀጣናዎች በመከታተልና በሙከራ ደረጃ በማህበረሰቡ እንዲጠበቁ በማድረግ፣ ከአካባቢ የመስተዳድር አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር የቅድመ መከላከል የግንዛቤ ሥራዎችን በማጠናከር የአስተሳሰብ ለውጦች እንዲመጡ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ 1 ሪጅን የተቋማዊ ደህንነት ፊዚካል ሴኩሪቲ ከፍተኛ መኮንን ኮሎኔል ተስፋዬ ነጋሽ እንደገለጹት ሪጅኑ የሚያስተዳድራቸውን መሠረተ ልማቶች ደህንነት ለማረጋገጥ ከቅድመ መከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ጀምሮ በጥብቅ ክትትል የሚያዙ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ቀርበው ፍርድ እንዲያገኙ ከአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
በሪጅኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በተካሄደባቸው አካባቢዎች ስለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ጥበቃ የተሻለ ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኮሌኔሉ ገለጻ ማህበረሰቡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች የተቋሙ ብቻ ሳይሆኑ የሀገር እና የህዝብ ንብረት መሆናቸዉን የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝ በመደረጉ በታወር ስርቆት የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ ተችሏል።
የደቡብ 1 ሪጅን የፊዚካል ሴኩሪቲ ከፍተኛ ባለሙያ ኮሎኔል ኤርሚያስ ደሳለኝ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በሪጅኑ በተለያዩ ቦታዎች በታወር ስርቆት ወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙ አስር ግለሰቦች መካከል ሦስቱ እንደተፈረደባቸው፤ ሌላ ሦስት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የክስ ሂደታቸው እየታየ እንደሆነና ቀሪ አራት ተጠርጣሪዎች ግን ምስክር በመጥፋቱ መለቀቃቸውን አስረድተዋል።
ኮሎኔሉ አክለውም የኤሌክትሪክ ኃይል ለሃገር ልማትና እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ በተቋሙ በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመከላከልና ተቋማዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በሪጅኖች የተመደቡ የፊዚካል ሴኩሪቲ ከፍተኛ መኮንኖች ስርቆትን ለመከላከል ከሪጅን የሥራ ኃላፊዎች፣ ከአካባቢው የመስተዳድር አካላት እና ከማህበረሰቡ ጋር የሚደረጉ ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠው ሥራቸውን የበለጠ ለማቀላጠፍ የተሽከርካሪ እና ሌሎች ግብዐቶች እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል።



የተቋማዊ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሺፋ የተቋሙን መሠረተ ልማት ደህንነት ለማረጋገጥ የፊዚካል ሴኩሪቲ ከፍተኛ መኮንኖች በስርቆት ክትትል፣ በቅድመ መከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ ፍርድ ለማሰጠት ባከናወኗቸው የትብብር ሥራዎች የተገኙ ለውጦችን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የተቋሙን መሰረተ ልማት ደህንነት ለማስጠበቅ በሁሉም ሪጅኖች ተግዳሮት የሆኑ የሎጅስቲክስ እጥረቶች እንዲፈቱ መምሪያው ጉዳዩ ከሚመለከተው ክፍሎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስረድተዋል።
የንብረትና ጠቅላላ አገልገሎት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ስመኝ አያሌው በበኩላቸው በተቋሙ የሚነሱ የተሽከርካሪ ችግሮችን ለመፍታት ጽ/ቤታቸው እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።




