ተቋሙ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጥ ስምምነት ተፈራረመ

ተቋሙ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጥ ስምምነት ተፈራረመ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዘላቂ አገልግሎትና የኃይል ምርት አስተማማኝ ለማረጋገጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ፡፡

ስምምነቱት የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የቮይት ሃይድሮ ሻንጋይ ግሩፕ የሃይድሮ ሰርቪስ ዳይሬክተር ዋን ጂይ ናቸው፡፡

በቻይና ሻንጋይ በሚገኘው የቮይት ሃይድሮ ሻንጋይ ዋና መሥሪያ ቤት የተከናወነው የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዓለም አቀፍ የውሃ ኃይል መፍትሔዎች አቅራቢ ከሆነው ቮይት ሃይድሮ ሻንጋይ ኩባንያ የረጅም ጊዜ የጥገና እና የቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎት ለማግኘት ያስችለዋል፡፡

ስምምነቱ በዋናነት ሁለት ወሳኝ የትብብር መስኮችን ያካተተ መሆኑን የገለፁት ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የግድቡን ከፍተኛ የኃይል ማመንጨት አቅም ታሳቢ ያደረገ የአቅም ግንባታ ሥራ እና የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት የስምምነቱ መሠረቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኦፕሬሽን እና ጥገና ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል ተከታታይ ሥልጠናዎችና የዕውቀት ሽግግር እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡

የስምምነቱ መተግበር ግድቡ በታቀደለት የሥራ ዘመን በሙሉ በብቃትና በአስተማማኝ ሁኔታ ኃይል እንዲያመነጭ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ ከአቅም ግንባታው ጎን ለጎን በስምምነቱ የተካተተው የረጅም ጊዜ የማዕቀፍ ስምምነት ለግድቡ የኃይል ማመንጫ ክፍሎች አስፈላጊ የሆኑ ኦሪጅናል የመለዋወጫ ዕቃዎችን በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ያስችላል፡፡

ስምምነቱ ማንኛቸውም ቴክኒካዊ ብልሽቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት ያለምንም መዘግየት ፈጣን ጥገናዎችን ለማካሄድና የግድቡን የሥራ ዝግጁነት ለማሳደግ ታላቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በቮይት ሃይድሮ ሻንጋይ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ለቀጣናው የኃይል ትስስር የሚጫወተውን ስትራቴጂካዊ ሚና በዘላቂነት ለማስቀጠል የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተመልክቷል።

Scroll to Top