ታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የገነባው የዊቢልድ  ግሩፕ የሳሞተር 2026 የፈጠራ ሽልማትን አሸነፈ

ታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የገነባው የዊቢልድ  ግሩፕ የሳሞተር 2026 የፈጠራ ሽልማትን አሸነፈ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዊቢልድ ግሩፕ የሳሞተር 2026 የፈጠራ ሽልማትን  (Samoter 2026 Innovation Award) አስገኝቷል።

በጣሊያን በተካሄደው የሳሞተር ዓለም አቀፍ የግንባታ ማሽነሪዎች ኤግዚቢሽን ላይ የተሰጠው ይህ ሽልማት  የፕሮጀክቱን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ፋይዳ እንዲሁም የኢትዮጵያንና የአፍሪካን የኃይል ዘርፍ ገጽታ በመለወጥ ረገድ ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳይ ነው።


በ1965 የተመሰረተው የሳሞተር የፈጠራ ሽልማት በአውሮፓ የግንባታ ምህንድስና ዘርፍ ውስጥ ረጅም ዕድሜ ካላቸውና ታዋቂ ከሆኑ የክብር ሽልማቶች አንዱ ሲሆን  ሽልማቱ በኃይል መሠረተ ልማት እና በኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ አነስተኛ የቴክኒክ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ አዲስና አብዮታዊ ለውጥን ያመጡ ፕሮጀክቶችን እውቅና ለመስጠት ያለመ ነው።


የህዳሴ ግድብን በመገንባቱ ዊ ቢልድ ግሩፕ ለሽልማት የተመረጠው ግድቡ በዓለም አቀፍ የብቃት መለኪያ እና በዘመኑ ከፍተኛ ለውጥ ካመጡ የሲቪል ሥራዎች አንዱ መሆኑን የሽልማት ኮሚቴው ካረጋገጠ በኋላ ነው። በተጨማሪም የሽልማት ኮሚቴው ፕሮጀክቱ ያለውን ጥልቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በአጽንዖት መገምገሙን አስታውቋል።
 

ግድቡ በግንባታ ላይ ከ25,000 በላይ ሠራተኞችን በማሳተፍ የሰው ኃይል ልማትን ለማፋጠን እንደ መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉንና ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ኮሚቴው አስታውቋል።

እነዚህ ዜጎች ለሀገሪቱ የወደፊት የኢንዱስትሪ ልማት ዘላቂ ሀብት የሚሆኑ ልዩ የቴክኒክ ክህሎቶችን ከመቅሰማቸውም  በላይ የግንባታው ስፍራ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የስፖርት መገልገያዎችን እና ቋሚ የጎዳና መረቦችን ጨምሮ አስፈላጊ የሲቪል መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል ሲል ገልጿል። ይህም ግድቡ የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለማህበራዊ ልማትም ትልቅ መሣሪያ መሆኑን አረጋግጧል።


የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡ የምህንድስና ተግባራት መካከል ይመደባል።

በ5,150 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ግድብ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ምርት አቅም በእጥፍ ለማሳደግ ታስቦ የተገነባ ነው።

ግድቡ ምንም ዓይነት የበካይ ጋዝ ልቀት ሳይኖረው ከሦስት መካከለኛ መጠን ካላቸው የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ጋር እኩል የሆነ የተረጋጋና ታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚያቀርብ ሲሆን ይህም በአህጉሪቱ የኃይል ሽግግር ሂደት ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።


በመሆኑም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የኃይል ሽግግር ወካይ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ለትላልቅ የውሃ ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች እንደ ዓለም አቀፍ መለኪያ ተደርጎ ይጠቀሳል።

Scroll to Top