በተቋሙ ንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል

በተቋሙ ንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በዘላቂነት ለመከላከል የሚደረገውን ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋማዊ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው ከሪጅን ኃላፊዎችና ከመሠረተ ልማት ደህንነት የጥበቃ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ደህንነት ዙሪያ የተከናወኑ ሥራዎችን አስመልክቶ ለሦስት ቀናት በሀዋሳ ሲያካሂድ የቆየውን ግምገማ አጠናቋል።

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሺፋ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት መምሪያው ከተደራጀ አጭር ጊዜ ቢሆነውም የተቋቋመበትን ተልዕኮ በሚገባ እየተወጣ ይገኛል።

መምሪያው በዘጠኝ ወራት ውስጥ ቢሮውን እና የሰው ኃይሉን ከማደራጀት ጀምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የኃይል ማመንጫ፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና ማስተላለፊያ መስመሮችን ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የታወር ስርቆትን በመከላከል ጥበቃውን ማጠናከር፣ የፊዚካል ሴኩሪቲ አቅምና ሽፋንን ማሳደግ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን የታቀዱ ተግባራት እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ በመምሪያው ስር ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡት የፊዚካል ሴኩሪቲ ከፍተኛ መኮንኖች ከሪጅን ኃላፊዎች ጋር በመተባበር በየደረጃው ካሉ የፌደራልና የክልል መስተዳድሮች እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት በመሰራቱ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በአምስት ሪጅኖች በሙከራ ደረጃ በማህበረሰብ ከሚጠበቁ 1 ሺህ 297 ታወሮች መካከል በ37ቱ የስርቆት ሙከራ ቢደረግም በ36 ታወሮች ላይ ሌቦቹ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ጠቅሰው በአካባቢው ማህበረሰብ ማስጠበቅ ትልቅ ውጤት ማስገኘቱን አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 4 ሺህ 498 የታወር ብረቶች ላይ የስርቆት ወንጀል ቢፈፀምም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ89 ነጥብ 9 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ጉዳት የደረሰባቸው የተቋሙ ንብረቶች አብዛኞቹ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው ሰሜን ሪጅን፣ ሰሜን ምዕራብ ሪጅን እና ሰሜን ምስራቅ አንድ ሪጅን የተፈጸሙ ሲሆኑ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ደቡብ 1፣ ደቡብ 2 እና ማዕከላዊ ሪጅኖች ስርቆቶች መፈፀማቸውን ጠቅሰዋል።

መምሪያው የመሠረተ ልማት ስርቆትን ከመከላከል ጎን ለጎን ባከናወናቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ከልማትና ከካሳ ይገባኛል ከቀረቡ 82 ቅሬታዎች በ71 ቅሬታዎች ላይ ምላሽ መሠጠቱን ገልጸዋል።

የየሪጅኑ የሥራ ኃላፊዎች እና የፊዚካል ሴኩሪቲ ከፍተኛ መኮንኖች ከአካባቢው የመስተዳድር የጸጥታ አካላት ጋር በጀመሯቸው የጋራ ጥረቶች የተገኙ ውጤቶችን እንዲያስቀጥሉም ነው ያሳሰቡት።

የመምሪያው የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ በደቡብ አንድ ሪጅን ከሀዋሳ – ይርጋለም በሚሄደው መስመር ላይ በስርቆት የወደቀ ታወርን እና የሀዋሳ ቁጥር ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያን ጉብኝት በማድረግ ተጠናቋል።

Scroll to Top