ጣቢያው ኃይል የማስተላለፍ ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ነው

ጣቢያው ኃይል የማስተላለፍ ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቃሊቲ አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል በማስተላለፍ የነበረውን ታሪካዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ እጅጉ ማሬ እንደገለጹት ማከፋፈያ ጣቢያው በሁለት ትራንስፎርመሮች በባለ 132 ኪሎ ቮልት ሦስት ገቢ መስመሮች ከቆቃ የመነጨውን ኃይል ተቀብሎ ለአቃቂ፣ ለጎፋ እና በጣቢያው ዙሪያ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ኃይል ለማስተላለፍ በ1950 ዎቹ የተገነባ ነው።

ጣቢያው የትራንስፎርመሮችን ቁጥር በማሳደግ ከቆቃ በተጨማሪ  በ 230 ኪሎ ቮልት ከመልካ ዋከና የኃይል ማመንጪ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ ለገፈርሳ፣ ለኮተቤ፣ ለአዲስ ሴንተር እና ለሰበታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በባለ 132 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ኃይል ሲሰጥ እንደነበረም ጠቁመዋል።

የኃይል ማመንጫዎች በየጊዜው እያደጉ መምጣታቸውን ተከትሎ የትራንስፎርመሮቹ ቁጥር በመጨመር  የመጫን አቅማቸውን ከ63 ሜጋ ቮልት አምፔር ወደ 125 ሜጋ ቮልት አምፔር ከፍ መድረጉንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ እጅጉ ገለጻ ጣቢያው አሁን ላይ በ 230 ኪሎ ቮልት አራት ገቢ መስመሮች፣  በ 132 ኪሎ ቮልት አስር፣ በ 45 ኪሎ ቮልት አንድ፣ በ 33 ኪሎ ቮልት አራት እንዲሁም በ 15 ኪሎ ቮልት አምስት ወጪ መስመሮች ሲኖሩት በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉት አብዛኞቹ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያው ታሪካዊ ሚናውን መወጣት በሚያስችል መልኩ የኃይል ፍላጎቱን ታሳቢ ያደረገ የአቅም ማሳደግ እና የማዘመን ሥራዎችን ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የቃሊቲ አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት 510 ሜጋ ዋት የመጫን አቅም አለው።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top