በጣቢያዎቹ የኃይል ምርቱን አስተማማኝነት የሚጨምሩ የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል

በጣቢያዎቹ የኃይል ምርቱን አስተማማኝነት የሚጨምሩ የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአዋሽ 2 እና 3 የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን የኃይል ምርት አስተማማኝነት የሚጨምሩ የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም መከናወናቸው ተገለጸ።

የጣቢያዎቹ የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ሮቤል አበበ  እንደገለጹት በማመንጫ ጣቢያዎቹ የቅድመ መከላከል፣ የትንበያ እና የፍተሻ ጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም በማከናወን ዩኒቶቹ የአቅማቸውን ከ95 በመቶ በላይ ኃይል እያመረቱ ይገኛል።

የአዋሽ ሦስት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የመቆጣጠሪያ ብሬከርን በመቀየር ቆሞ የነበረው ተርባይን እንዲሰራ በማድረግ የኃይል ምርቱን አስተማማኝነቱን ማስጠበቅ መቻሉን ገልፀዋል።

በአዋሽ ሁለት ጣቢያ ከአሁን ቀደም የነበሩ መቆጣጠሪያ ብሬከሮች ረጅም ጊዜ ያገለገሉና የተለያዬ ጉዳት የደረሰባቸው እንደነበሩ የጠቆሙት አቶ ሮቤል ከአዋሽ 7 ኪሎ ዲዝል ጣቢያ የነበረን ብሬከር በማምጣት ተከላ ተጠናቆ የሙከራና የፍተሻ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ባለ 15 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያ ብሬከሮችን ሙሉ በሙሉ በአዲስ በመቀየር ወደ አገልግሎት ማስገባት መቻሉንም አብራርተዋል።

የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም መከናወናቸው ጣቢያዎቹ ለረጅም ዓመት አስተማማኝ ኃይል እንዲያመርቱ ከማስቻሉም በላይ ጊዜንና ወጪን በመቆጠብ የሠራተኞች ቡድናዊ ስሜት እንዲጠነክር እና እርስ በእርስ ልምድ በመለዋወጥ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበትን ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የአዋሽ 2 እና 3 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አበበ በበኩላቸው ጣቢያዎቹ 64 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ኖሯቸው ከ60 ዓመት በፊት ኦፕሬሽን ቢጀምሩም ዛሬም ከ56 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እያመነጩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ጣቢያዎቹ የተሰሩት የቆቃ ኃይል ማመንጫ ግድብን ተከትለው በመሆኑ ከቆቃ በሚለቀቀው የውሃ መጠን የበጀት ዓመቱን የኃይል ምረት እቅድ ለማሳካት እየሰራ ነው።

ተርባይኖች እንዳይቆሙ ዕቃዎች ላይ ማሻሽያ በመስራት በራስ አቅም በርካታ የጥገና ሥራዎችን እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ጣቢያዎቹ ረጅም ዓመት ያገለገሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የመልሶ ግንባታ ሥራ የሚፈልጉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የጥገና ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወን ባለሙያዎቹ አጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ የእርስ በእርስ መማማሪያ ሥርዓት መዘርጋቱም ጠቁመዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top