የማከፋፈያ ጣቢያው የፍተሻና የሙከራ ሥራ በስኬት ተጠናቋል

የማከፋፈያ ጣቢያው የፍተሻና የሙከራ ሥራ በስኬት ተጠናቋል

የመቱ ማሻ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የፍተሻና የሙከራ ሥራ በስኬት መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ አሸናፊ ሙሉብርሃን እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያው ከዓለም  ባንክ በተገኘ 7 ሚሊዮን ዶላር ብድር  እና ተቋሙ በመደበው አንድ ቢሊየን ብር  ለማሻና ለአካባቢው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን የኃይል ትስስር ለማሳለጥ ህዳር 2012 ዓ.ም ነበር ግንባታው የተጀመረው።

የማከፋፈያ ጣቢያው የፍተሻና የሙከራ ሥራ ትናንት በስኬት ተጠናቆ በዛሬው ዕለት ትራንስፎርመሩን ሥራ የማስጀመር ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 50 ሜጋ ቮልት አምፔር የመሸከም አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች እንዲሁም ስድስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ የመብራት አቅርቦት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ የሀብቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይቷል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያው ሥራ መጀመር የማሻ ከተማና አካባቢው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያነቃቃ አስረድተዋል።

የመቱ ማሻ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታውን ሲኖ ሃይድሮ ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ኩባኒያ ሲያከናውን በአማካሪነት ደግሞ ኢ. ኤል. ሲ. ELC የተባለ የጣሊያን ኩባንያ ተሳትፎበታል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top