በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቆቃ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግድብ በ2017 በጀት ዓመት ለማመንጨት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል የውሃ መጠን መያዙን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሞርካ ኃይሌ እንደገለጹት ከአባ ሳሙኤል ቀጥሎ በ1952 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የቆቃ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላለፉት 65 ዓመታት አስተማማኝ ኃይል እያመረተ ይገኛል።
ማመንጫ ጣቢያው በ2017 በጀት ዓመት 134 ነጥብ 9 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማምረት አቅዶ በ9 ወራት ውስጥ 119 ጊጋ ዋት ስዓት ኃይል ማምረቱን ጠቁመዋል።
ከግድቡ የሚለቀቀው ውሃ በሕብረተሰቡ ላይ የጎርፍ አደጋ እንዳይደርስ እንዲሁም ከማመንጫው በታችኛው ተፋሰስ ለሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ለመልቀቅ በግድቡ የሚገኘው ውሃ በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር እና በአዋሽ ተፋሰስ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
አሁን ላይ በግድቡ ያለው የውሃ መጠን ከባህር ጠለል በላይ 1586 ነጥብ 68 ሜትር ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከባህር ጠለል በላይ 1587 ነጥብ 01 ሜትር እንደነበር አውስተዋል።
በግድቡ ውስጥ የሚገኘው የውሃ መጠን ጣቢያው በቀሪ ወራት ያለምንም የውሃ እጥረት ኃይል እንዲያመነጭና ዓመታዊ ዕቅዱን እንዲያሳካ የሚያስችለው መሆኑን አቶ ሞርካ ተናግረዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ዕቅዱን ለማሳካት ከውሃ አስተዳደር ሥራው ጎን ለጎን ሣምንታዊና ወርሃዊ የጥገና ሥራዎች በዕቅድ ተይዘው በመከናወን ላይ ናቸው።
ጣቢያው ከ65 ዓመታት በኋላም ሲገነባ ከተቀመጠለት 110 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ አማካይ ዓመታዊ የኃይል ምርት እያመረተ መሆኑን ገልፀው ለዚህም የኦፕሬሽንና የጥገና ክፍሉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከ25 ዓመት በፊት በኤሌክትሮ ሜካኒካል ክፍሉ ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ መከናወኑን የጠቆሙት አቶ ሞርካ አሁንም ጣቢያው ረጅም ዓመት ከማገልገሉ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ክፍሎች ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል።
የግድቡን ደህንነት ለመጠበቅና የእምቦጭ አረምን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በዕቅድ ተይዞ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የቆቃ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሦስት ተርባይን 43 ነጥብ 2 ሜጋ ዋት የማምረት አቅም አለው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

