የደቡባዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የንባታ አጠቃላይ አፈፃፀም 65 በመቶ ላይ መድረሱን በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ሱፐርቫይዘር ተናገሩ።
ሱፐርቫይዘሩ አቶ ተመስገን ጥላሁን እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ከወላይታ ሶዶ 2ኛ እና በግንባታ ላይ ከሚገኘው የሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያዎች በሁለት ገቢ መስመሮች ኃይል ተቀብሎ በአስር ባለ 33 እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ለደንበኞች ኃይል ለማቅረብ እየተገነባ ይገኛል።
ማከፋፈያ ጣቢያው ሁለት የባለ 125 አውቶ ትራንስፎርመሮች፣ ሁለት ባለ 63 እና ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች የተከላና ገጠማ ሥራዎች እንዲሁም ዘይት የመሙላት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች መትከያ፣ የፕሮቴክሽንና ሌሎች የኮሙዩኒኬሽኝ ገመዶች የሚዘረጉበት የመሠረት ሥራ እንዲሁም የ230 እና 132 ኪሎ ቮልት የሲዊች ያርድ የስቲል ስትራክቸር ተከላ ሥራዎች ሲጠናቀቁ የ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች የስቲል ስትራክቸር ሥራ ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚኙ አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።
የመቆጣጠሪያ ቤቱ የግንባታ ሥራ 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን የኦፕሬተሮች የመኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሥራ እየተፋጠነ እንደሆነም ተናግረዋል።
የመቆጣጠሪያ ክፍሉንና የፕሮቴክሽን ፓናሎች ገጠማና ገመድ ዝርጋታ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን፣ የፍተሻና ሙከራ እንዲሁም ሌሎች የተጀመሩ ቀሪ ሥራዎችን በቀጣዮቹ ስምንት ወራት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ሱፐርቫይዘሩ አስረድተዋል።
እንደ ሱፐርቫይዘሩ ገለፃ የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ 68 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ 40 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ አፈፃፀሙ ደግሞ ከ65 በመቶ በላይ ደርሷል።
በአካባቢው ያለውን ግሪድ ስርዓት ለማጠናከር የማከፋፈያ ጣቢያውን ከአርባ ምንጭ 1ኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል የማስፋፊያ ሥራ በነባሩ ላይ መጀመሩንም ጠቁመዋል።
ከ37 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ የሚገኘው የአርባ ምንጭ 2ኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በከተማዋ አካባቢ ሊገነባ ለታሰበው የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪ ፓርክ እና በ120 ኪሎ ሜትር ውስጥ ለሚገኙ አካባቢዎች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



