የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚመጥን የኃይል መሰረተ ልማቶችን ግንባታ እያካሄደ መሆኑን የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር ገለጹ።
ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ኢኮኖሚያዊ እድገትንም ሆነ ማህበራዊ ልማት ፈጽሞ ማሰብ የማይቻልበት ጊዜ ሆኗል።
ተቋሙም ይህን ታሳቢ ያደረጉ የኃይል መሰረተ ልማቶችን ግንባታ በመላ ሀገሪቱ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ያለውን ሀገራዊ ኃይል የማመንጨት አቅም ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ አምስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ተጨማሪ የኃይል ፍላጎት ባለባቸው አካባቢዎች የማከፋፈያ ጣቢያዎች የማስፋፊያና የማዘመን ሥራ ከማከናወን ጎን ለጎን ተደራሽነቱንና ፍትሐዊነቱን የሚያሰፉ አዳዲስ የማከፋፈያ ጣቢያዎችንና ማስተላለፊያ መስመሮችን እየገነባ እንደሆነም ተናግረዋል።
የሚገነቡ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የማስተላለፊያ መስመሮች እስከ አሁን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያልነበሩትን አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግን ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የኃይል ተደራሽነት ሽፋኑን አሁን ካለበት 54 በመቶ ወደ 78 በመቶ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሞገስ ገልፀዋል።
ከዋናው ግሪድ ኃይል የማያገኙ አካባቢዎችም ኦፍ ግሪድ በሆነ ወይም ከግሪድ ጋር ባልተገናኘ መንገድ ኃይል የሚያገኙበትን መንገድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገርም በቀጣናው የሚገኙ የጎረቤት ሀገራትን በኃይል ለማስተሳሰር በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በዚህም ለጅቡቲ፣ ለኬኒያና ለሱዳን ኃይል እየቀረበ መሆኑንና በቅርቡም ለታንዛኒያ ማቅረብ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ ለጎረቤት ሀገራት እየቀረበ ያለው ኃይል ከሚመነጨው ከ10 በመቶ በታች ድርሻ ቢኖረውም የተቋሙን ከ30 በመቶ በላይ ገቢ እየሸፈነና ለቀጣናዊ ትስስር አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
እየተገነቡ ያሉ የኃይል መሰረተ ልማቶች የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 የቀረፀውን አህጉሩን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ዕቅድ ለማሳካት ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክቱ ነው ያብራሩት።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በኦፕሬሽን ላይ ብቻ የሚገኙ 194 የማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ 20 ሺ 673 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመሮች እና 17 የማመንጫ ጣቢያዎችን ያስተዳድራል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




