ጣቢያው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ5 ሺ 430 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል

ጣቢያው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ5 ሺ 430 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል አመንጭቷል

የጊቤ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዕቅዱ በላይ ኃይል ማምረቱን የጣቢያው የኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ደጀኔ ጉታ እንዳስታወቁት ማመንጫ ጣቢያው በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 4 ሺ 725 ነጥብ 56 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለማመንጨት አቅዶ 5 ሺ 436 ነጥብ 5  ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ችሏል፡፡

ይህም ከዕቅዱ የ710 ነጥብ 94 ጊጋ ዋት ሰዓት ወይም የ15 ነጥብ 04 በመቶ እንዲሁም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ189 ነጥብ 65 ጊጋ ዋት ሰዓት ወይም የ3 ነጥብ 61 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን አቶ ደጀኔ ተናግረዋል፡፡

አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት የሚያስችሉ የፍተሻና የክትትል ሥራዎች በየጊዜው መከናወናቸው፣ የኦፕሬሽን ሥራው የተቋሙ ሥራ አመራር ባፀደቀው የኦፕሬሽን ሥራዎች የአሰራር ስርዓት ማኑዋል መሰረት መከናወኑ እና የኃይል መቋረጥ አመላካቾችና ችግሮች (alarms and faults) ሲስተዋሉ ወዲያውኑ እንዲወገዱ መደረጋቸው ጣቢያው ከዕቅዱ በላይ ለማመንጨቱ ምክንያቶች እንደሆኑ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 6 ሺ 141 ነጥብ 49 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ያስታወሱት አቶ ደጀኔ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከአጠቃላይ ዕቅዱ የ88 ነጥብ 52 በመቶ አፈጻፀም ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህም በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አመላካች እንደሆነ አስታውቀዋል                                                                                                   

የጊቤ 3 ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ18 ማመንጫ ጣቢያዎች ከተመረተው የ21 ሺ 299 ነጥብ 69 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ የ25 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ በመያዝ የታላቁ ህዳሴ ግድበን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ከኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top