የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግሪድ ማዘመን፣ የዲጂታላዜሽን፣ ታዳሽ ኃይልን የማመንጨት እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡
በፕሮጀክቶቹ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት ተቋሙ ለሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች አበዳሪ ተቋማት ለሰጡት ትኩረት እና ላሳዩት ፈጣን ምላሽ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።


በፕሮጀክቱ ታዳሽ የሆነና የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የኃይል አማራጮች ማልማት እና በተቋሙ ውስጥ ባሉ ሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ዲጂታላይዝድ የሆኑ አሰራሮችን መተግበር እንደሚያካትት አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተጠሪና የትብብር ኃላፊ ሚስተር ሮቤርቶ ሽሊሮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የውሃ ኃይል ማመንጫ መሰረተ ልማት በመገንባት ብትታወቅም ያልተነኩ የፀሐይ፣ የንፋስ እና የጅኦተርማል እምቅ ሀብቶች ባለቤት እንደሆነች መገንዘባቸውን አንስተዋል፡፡


ስለሆነም ህብረቱ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን የተቋሙን የልማት ሥራዎች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የትራንስሚሽን ቢዝነስ ፕሮግራም 3 ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ተፈራ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ ተቋሙን ወደ ተሻለ ቁመና ለማድረስ ታስበው የተቀረፁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በተቋሙ በአምስት ዓመት የሚተገበሩት ፕሮጀክቶች በአራት ዘርፎች ማለትም የግሪድ ማዘመንና ዕድሳት፣ ዲጅታላዜሽን፣ ታዳሽ ኃይል ልማት እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡
ፕሮጀክቶቹን ለማስፈፀም 270 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚፈልግ የጠቀሱት ሥራ አስኪያጇ የፋይናንስ ምንጩ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና የፈረንሳይ ግምጃ ቤት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአምስት ዓመት የሚጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት 22 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ የማዘመን ሥራ፣ አዲስ የመቆጣጠሪያ ማዕከል/NlDC/ ግንባታ፣ የትራንስፎርመር ወርክ ሾፕ እድሳት፣ የ1 ሺህ 590 ኪሎ ሜትር የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ዝርጋታ እና ደረጃውን የጠበቀ የሥልጠና ማዕከል ግንባታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ሥራ አስኪያጇ አብራርተዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የተጎዱ የአሸጎዳ የንፋስ ተርባይኖችን በመጠገን ወደ ኦፕሬሽን ለመመለስ መታቀዱንም አመልክተዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

