በኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ የተራቆቱ ቦታዎችን ቀድሞ ወደነበሩበት ተፈጥሯዊ ይዞታ የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በፕሮጀክቱ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዕቅድ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ እንዳስታወቁት ፕሮጀክቱ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳይ ሥራዎችን በአካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ምክረ ሃሳብ እና በሳይት የመልሶ ማልማት የአሰራር ሥርዓትና ዕቅድ መሰረት እያከናወነ ነው፡፡
በዚህም ለፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ግብዓት የተቆፈሩ እና ተረፈ ምርቶች ተጠራቅመውባቸው የነበሩ የተለያዩ ቦታዎችን በጥናቱና በአሰራር ስርዓቱ መሰረት ወደ ተፈጥሯዊ ይዞታቸው የመመለስ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ ግዛቸው እንዳሉት ፕሮጀክቱ ራሱን የቻለ የሥራ ቡድን እና የችግኝ ጣቢያ አቋቁሞ ከግንባታ ሥራው ጎን ለጎን የመልሶ ማልማት ሥራውን የዕለት ተዕለት ተግባራት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡
ሥራው ለአካባቢው መልክዓምድር እና ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ ሀገር በቀል ችግኞችን እና የአፈር መከላትን መከላከል እንደሚያስችል በሳይንሳዊ ዘዴ የተረጋገጠ “ቪቲባር” የተሰኘ ሳርን በመትከል እየተከናወነ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
የተለያዩ ማሽነሪዎችና ወርክ ሾፖች የተተከሉበት ቦታን ጨምሮ በፕሮጀክቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ቀሪ ቦታዎችን ወደ ነበሩበት የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ግዛቸው አረጋግጠዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ለማጠናከር በሀገሪቱ በየዓመቱ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ እና በጣቢያው ላይ የሚያለማቸውን ችግኞችና ሳሮችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች እና መስተዳደሮች በማቅረብ አሻራዉን እያሳረፈ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአካባቢው ያለውን የመሰረት ልማት እጥረት ለመቅረፍ በመንገድ፣ በመጠጥ ውሃ፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን ማከናወኑን አቶ ግዛቸው አስረድተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ ዊቢውልድ ኩባንያ ኢንቫይሮመንታል ኢንጅነር የሆኑት አቶ ይኸነው ቸኮል በበኩላቸው እየተከናወነ ካለው የሳይት መልሶ ማልማት ሥራ በተጨማሪ አካባቢውን ከከባቢ አየር ብክለት ለመጠበቅ በቆሻሻና ተረፈ ምርት አወጋገድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ አካባቢውን ከብክለት ለመጠበቅ የሚያስችሉ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከተሸከርካሪና ማሽነሪዎች እጥበትና የሰርቪስ አገልግሎት የሚለቀቁ ዘይቶችና ዘይት ነክ ኬሚካሎች አካባቢውን እንዳይበክሉ ውሃውን ከዘይት የሚለይና የሚያጣራ ማሽን በመጠቀም ውሃው መልሶ ጥቅም ላይ የሚውልበት አሰራር መዘርጋቱን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኮንክሪት ሙሌት በሚከናወንበት ጊዜ የሚፈጠሩ የተረፈ ምርት ቆሻሻዎች አካባቢን የሚበክሉ መሆኑናቸውንና አለመሆናቸውን ናሙና በመውሰድ እንደሚረጋገጥና ጉዳት የሚያደርስ ከሆነም በሳይንሳዊ ዘዴ ተጣርቶ እንደሚለቀቅ ነው የጠቆሙት፡፡
የመልሶ ማልማት ሥራው የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ እና በቀጣይ ሰው ሰራሽ ሀይቁ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ ግድቡ የሚጠበቅበትን አገልግሎት በአግባቡ እንዲሰጥ ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




