በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ጉዳት የደረሰበትን የአላማጣ – አሸጎዳ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በአዲስ ኮንዳክተር የመቀየር ሥራ እያከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ህንፃ አረጋዊ እንዳስታወቁት የኮንዳክር ገመድ የመቀየር ሥራው ከ40 በመቶ በላይ ተከናውኗል።
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር በመጎዳቱ ምክንያት የኃይል መቆራረጥ በተደጋጋሚ ይከሰት እንደነበር የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ በግሪድ ኔትወርኩ ላይም አሉታዊ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ከአላማጣ – አሸጎዳ የተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር 126 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቢሆንም ከዚህ ውስጥ በአዲስ የኮንዳክተር ገመድ ለመቀየር የታሰበው 30 በመቶውን ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት።
መስመሩን ለመቀየር የሚያስፈልጉ 38 ድራም የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ እና የሚዘረጋውን የኮንዳክተር ገመድ የሚያገናኙ 100 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ማገናኛዎች (Mid Span Joint) መረከባቸውን አቶ ህንፃ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ መልክ የኮንዳክተር ዝርጋታ መከናወን ካለበት 37 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ውስጥ 15 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መጠናቀቁንም ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት።
እንደ አቶ ህንፃ ገለፃ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሶሶዎቹ የተዘረጉበት አካባቢ በረሃማና የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ አስቸጋሪ መሆን፣ ስርቆት እና የነዳጅ አቅርቦት ችግሮች የኮንዳክተር ገመድ ቆየራ ሥራውን ፈታኝ አድርገውታል።
የኮንዳክተር ሽቦ እና የኦ.ፒ.ጂ. ደብሊው ፋይበር መስመር ዝርጋታው ሲጠናቀቅ ከኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች መረጃዎችን ማግኘት ስለሚቻል በፍጥነት የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ሚናው የጓላ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ ቅየራ ሥራው በሪጅኑ አቅም እንዲከናወን በመወሰኑ ከፍተኛ ወጪ ማዳን ተችሏል ያሉት አቶ ህንፃ የዝርጋታ ሥራው እንዲሰራ ዕድሉን ላመቻቹ በየደረጃው ለሚገኙ የተቋሙ የሥራ አመራሮች ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





