የፊንጫ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ለማመንጨት ካቀደው የ17 በመቶ ብልጫ ያለው ኃይል ማምረቱን የጣቢያው ኃላፊ ገለፁ።
ኃላፊው አቶ ታደስ ፍቃዱ እንደገለፁት በግማሽ ዓመቱ 348 ጊጋ ዋት ሠዓት ኃይል ለማመንጨት አቅዶ 409 ነጥብ 3 ጊጋ ዋት ሠዓት ኃይል በማምረት የዕቅዱን 117 ነጥብ 62 በመቶ አሳክቷል።
ቀደም ሲል በጣቢያው የማቀዝቀዣ ሥርዓት ተፈጥሮ የነበረው ችግር በኃይል ማመንጨት ሥራው ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል።
ይሁንና የማቀዝቀዣ ሥርዓቱ በግማሽ ዓመቱ በራስ ኃይል በመጠገኑ ለኃይል ማመንጨት አፈፃፀሙ ከፍ ማለት አስተዋጽዖ ማበርከቱን አመልክተዋል።
በራስ ኃይል የተከናወነው የጥገና ሥራ ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ እንዳዳነው የጠቆሙት አቶ ታደሰ ይህ ሥራ በውጭ ተቋማት ቢከናወን ኖሮ የባለሙያ እና የዕቃ ግዥን ጨምሮ 22 ሚሊዮን ብር ያስወጣ እንደነበር አስታውቀዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ የጣቢያውን ዩኒቶች ደህንነት ለማረጋገጥ የፍተሻና ጥገና ሥራዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሠረት በአግባቡ ተከናውነዋል።
በአሁኑ ወቅት በግድቡ ላይ ያለው የውሃ መጠን በቀሪ ወራት ለማመንጨት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በ1967 ዓ. ም ኃይል ማመንጨት የጀመረው የፊንጫ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 134 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



