ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት በስርቆት ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሶበታል

ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት በስርቆት ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሶበታል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶ ብረቶችና ሽቦዎች ስርቆት ምክንያት ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው  ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንደገለጹት በኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎች የተቋሙ ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሆነዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 16 የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎች በስርቆት ምክንያት መውደቃቸውን እና በስርቆቱ ከ92 ነጥብ 32 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 43 ሺ 671 ብረቶች መሰረቃቸውንም ተናግረዋል።

የወደቁ የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎችንና የተሰረቁ የኮንደክተር ሽቦዎችን መልሶ ለመተካት ከ34 ነጥብ 35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን የጠቆሙት አቶ ዋለ ባለፉት በስድስት ወራት ብቻ በስርቆቱ ምክንያት ሳይሸጥ የባከነውን ኃይል ሳይጨምር ተቋሙ በአጠቃላይ ከ126 ነጥብ 81 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዋለ ገለፃ በበጀት ዓመቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ሠፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመከናወናቸው ምክንያት በኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ ይፈፀሙ የነበሩ የስርቆት ወንጀሎች ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅቶች ጋር ሲነጻጸር መቀነስ አሳይቷል፡፡

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር የሥራ ክፍልን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።

የሥራ ክፍሉን በቁሳቁስና በሰው ኃይል ለማደራጀት እየተሰራ እንደሆነና በክልል ከተሞች ጭምር መዋቅሩን ለመዘርጋት በቅጥር ሂደት ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡

የክፍሉ መደራጀት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎችን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቁ የሚያስችል ሠፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመስራት እንደሚያግዝ  ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቶችን ሳይጨምር በተቋሙ 41 ሺ 747 የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎች በኦፕሬሽን ላይ ይገኛሉ፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top